News Detail

National News
Mar 01, 2024 1.3K views

በአፍሪካ 9ኛው በኢትዮጰያ አምስተኛው የትምህርት ቤት ምገባ ቀን በድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ተከበረ፡፡

በአፍሪካ 9ኛው በኢትዮጰያ አምስተኛው የትምህርት ቤት ምገባ ቀን " ለሀገር በቀል የትምህርት ቤት ምገባ መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስ ለተሻለ ትውልድ ግንባታ!!" በሚል መሪ ቃል በሀገር ደረጃ በድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ተከበረ፡፡
በትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አየለች እሸቴ በበዓሉ ላይ ተገኝተው የትምህርት ቤት ምገባ ወጪ ሳይሆን በመጪው ሀገር ተረካቢ ትውልድ ላይ የሚደረግ አዋጭና ዘላቂ የሰብዓዊ ልማት ኢንቨስትመንት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
መርሃ-ግብሩ በአግባቡ ከተተገበረ የልጆችን አካላዊና አዕምሮኣዊ ዕድገት በማፋጠንና ጤንነታቸውን በመጠበቅ የተማሪዎችን የትምህርት ውጤታማነት እንዲሻሻል በማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለውም ጠቁመዋል፡፡
ክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ የትምህርት ቤት ምገባ እንደሃገር በመንግሰት ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት እየተተገበረ ያለና ከ6.2 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች ተጠቃሚ ያደረገ ፕሮግራም መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም የመንግስት አካላት፣የልማት አጋሮች፣ የግሉ ዘርፍ ባለሀብቶችና ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች የነገ ሀገር ተረካቢ የሆኑ ታዳጊዎችን ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ለመገንባት በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን ጥረት ለመደገፍ እያበረከቱ ላሉት አስተዋጽኦ አመስግነው በቀጣይም ድጋፋቸውን ይበልጥ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከዲር ጁሃር በበኩላቸው ከተማ መስተዳድሩ ለትምህርት ቤት ምገባ ከፍተኛ ትኩረት ስጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የአለም ምግብ ፕሮግራም ተወካይ ሚስተር ኤልቪስ ኦድኬ ኢትዮጵያ በዚህ አመት በትምህርት ቤት ምገባ መርሃ-ግብር 6.2 ሚሊዮን ተማሪዎችን ተጠቃሚ በማድረግ በግንባር ቀደምትነት የምትጠቀስ መሆኑዋን ጠቅሰው በቀጣይም እ.አ.አ. በ2030 ሁሉንም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የምገባ መርሃ ግብር ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራች ያለችው ስራ ስኬታማ እንዲሆን ተቋማቸውም የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ገልጽዋል፡፡
በክብረ በዓሉ ላይ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የክልልና ከተማ መስተዳደር ትምህርት ቢሮ፥ የሴክተር መ/ቤቶች ተወካዮችና አመራሮች፥ ሌሎችም ባለድርሻና አጋር አካላት እንዲሁም የዴሬደዋ ከተማ መስተዳደር አመራሮች፥ የአከባቢው ማህበረስብ ተወካዮች የተሳተፋ ሲሆን ስኬታማ የትምህርት ቤት ምገባ ስራዎች ተጎብኝተዋል ።
Recent News
Follow Us