News Detail
Jul 23, 2025
121 views
የመምህራንና የትምህርት አመራሮች ብቃትና ተነሳሽነት ለትምህርት ጥራት ወሳኝ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አየለች እሸቴ አስገነዘቡ፤
ከመጪው ሐምሌ 28 ጀምሮ ከ84 ሺ በላይ ለሚሆኑ የሁለተኛ ደረጃ መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች ልዩ የክረምት የአቅም ግንባታ ስልጠና እንደሚሰጥ ተገለጸ።
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አየለች እሸቴ በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርስቲ የተጀመረውን የአሰልጣኞች ስልጠና ሲከፍቱ እንደገለጹት የመምህራንና የትምህርት አመራሮችን ብቃትና ተነሳሽነት ማሳደግ ለትምህርት ጥራት ወሳኝ መሆኑን አስታውቀዋል።
መምህርነት ዜጋን በዕውቀት፣ በክህሎትና በሥነምግባር በማነጽ ተምህርት የሚያስጨብጥና ዜጎች ችግር ፈቺ ፣ተመራማሪ፣ ሀገር ተረካቢና ገንቢ እንዲሆኑ የሚቀርጽ ሙያ መሆኑን አስገንዝበዋል።
መምህርነት ቅድመ ሁኔታዎች ሳይገድቡት የወላጅነትና የባለአደራነት ሚና የሚወጣ የሙያዎች ሁሉ ቁንጮ በመሆኑ መምህራን የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት እንዲወጡና የተማሪዎች ውጤት እንዲሻሻል የትምህርት ቤት አመራሮቾ ከፍተኛ ድርሻ አላቸው ብለዋል።
የትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በሥርዓተ ትምህርት ፣በመምህራንና አመራሮች ልማት፣ትምህርት ቤቶችን ምቹ በማድረግና ሌሎች በርካታ ስራዎችን በማከናወን ላይ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ የመምህራንና የትምህርት አመራሮችን ብቃት ለማሳደግ ባለፈው ዓመት በተሰጠው ስልጠና ከተወሰዱ ልምዶች በመነሳት የታዩ ክፍተቶችን ሊቀርፉ የሚችሉ ስልቶችን በመንደፍ ከመጪው ሐምሌ 28 ጀምሮ ለ2ኛ ጊዜ ከ84 ሺ ለሚበልጡ መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች ስልጠና እንደሚሰጥ የገለፁ ሲሆን የዛሬው የአሰልጣኞች ስልጠና መርሃ ግብር ተሳታፊዎችም የተጣለባቸውን ትልቅ አገራዊ ተልዕኮ በብቃት እንዲወጡም የአደራ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ብርሃነ መስቀል ጠና በበኩላቸው የትምህርት ስብራትን ለማከምና ትውልድን ለማነጽ መምህራን ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።
የመምህራንና የትምህርት አመራሮች ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ሙሉቀን ንጋቱ በበኩላቸው የአሰልጣኞች ስልጠናው ዓላማ የመምህራንንና የትምህርት አመራሮችን አቅምና ብቃት በማሳደግ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል መሆኑን አስታውቀዋል።
የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት መምህራንና የትምህርት አመራሮች ስልጠና ለሁለተኛ ጊዜ መዘጋጀቱን ጠቁመው ባለፈው ዓመት የተሰጠው ስልጠና ጠቃሚ ልምድና ተሞክሮ መገኘቱንም አብራርተዋል።
ዛሬ በተጀመረውና ለሦስት ቀናት በሚቆየው ልዩ የክረምት መምህራንና የትምህርት አመራሮች የአሰልጣኞች ስልጠና ከ30 ዩኒቨርስቲዎች የተውጣጡ 630 ምሁራን ተሳታፊ ሆነዋል።
Recent News
Jul 11, 2025