News Detail
Jan 31, 2026
22 views
በከፍተኛ ትምህርት የሚስተዋለውን በሦስተኛ ዲግሪ (PhD) የሰለጠነ የሰው ሀይል እጥረት ለማቃለል እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ።
በህንድና በኢትዮጵያ ትምህርት ተቋማት የ3ኛ ዲግሪ ስልጠና ለመስጠት በተደረሰው ስምምነት አተገባበር ዙሪያ ውይይት ተደርጓል።
የአካዳሚክ ጉዳዮች መሪ ስራ አስፈጻሚ ኤባ ሚጀና(ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት በአገሪቱ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በ3ኛ ዲግሪ (PhD) ያለው የሰለጠነ የሰው ሀይል ከ18 በመቶ እንደማይበልጥ ተናግረዋል።
ለአገር ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በሚያበረክተው የኢንጂነሪንግና ቴክኖሎጂ ዘርፍ በዶክትሬት ዲግሪ ደረጃ በአግባቡ የሰለጠነ የሰው ሃይል ለማፍራት እየተሰራ መሆኑን ዶክተር ኤባ ገልጸዋል።
በኢንጂነሪንግና በቴክኖሎጂ አድቫንስድ ከሆኑ የህንድ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቶች Indian Institutes of Technology በተደረሰ ስምምነት መሠረት በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ከ1200 የሚበልጡ መምህራንን ለማሰልጠን መታቀዱን መሪ ስራ አስፈጻሚው አመልክዋል።
የመምህራንና የተማሪዎች ጉዳይ ዴስክ ኃላፊ አቶ በየነ ተዘራ በበኩላቸው ከህንድ የትምህርት ተቋማት ጋር በተደረሰው ስምምነት መሠረት ከዚህ ዓመት ጀምሮ ለአምስት ዓመታት በየዓመቱ 252 የዩኒቨርስቲ መምህራን በ3ኛ ዲግሪ እንደሚሰለጥኑ አስታውቀዋል።
የፕሮግራሞችና ስርዓተ ትምህርት ዴስክ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ነገዎ በበኩላቸው በኢንጂነሪንግና በቴክኖሎጂ ዘርፍ በ3ኛ ዲግሪ ደረጃውን ጠብቆ የሚሰጠው ስልጠና የዘርፉን ተደራሽነት እንደሚያሳድገው ጠቅሰዋል።