History

የኢትዮጵያ ትምህርት ዳራ

በኢትዮጵያ ውስጥ ለዘመናዊ ትምህርት መጀመር እንደ መሸጋገሪያ ድልድይ ሆኖ ያገለገለው ለዘመናት በክርስትናና በእስልምና የሃይማኖት ተቋማት ሲሰጥ የነበረው የማንበብና የመፃፍ ትምህርት ነው፡፡ በዚህም የሃይማኖት  ትምህርቱን ከዘመናዊ ትምህርት ጋር በማጣጣም ብዙ የተማሩ ሰዎችን ማፍራት ችለዋል፡፡

 

ዘመናዊ ትምህርት ወደ ኢትዮጵያ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በተለያዩ የውጭ ሀገር ሰዎች በዋናነት በሚሲዎናውያን እንደገባ ይታመናል፡፡ የመጀመሪያው ዘመናዊ ትምህርት ቤት በ1900 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ዳግማዊ ምኒልክ  ትምህርት ቤት የሚል ስያሜ ተሰጥቶት ተጀመረ፡፡ 

 

ትምህርትን ወደ ሌሎቹም የሀገሪቷ ክፍሎች ለማስፋፋት አጼ ሚኒሊክ የተለያዩ እርምጃዎችን የወሰዱ ሲሆን ከነዚህም መካከል የሉዕካን ቡድን ወደ ውጭ ሀገራት በመላክ የሌሎች ሀገራትን የትምህርት ልማት ልምዶችን ቀስመው እንዲመጡ የተደረገበት እና ብዙ ተማሪዎችን ወደ አውሮፓ ሀገራት በመላክ የአውሮፓውያንን ትምህርት እንዲማሩ መደረጉን ማንሳት ይቻላል። በዚህም መሠረት በአጼ ሚኒሊክ ዘመን  ተጨማሪ ትምህርት ቤቶች በአንኮበር ሙቅ ምድር አካባቢ፣በደሴ ወ/ሮ ስህን እንዲሁም በአዲስ አበባና  በድሬዳዋ ከተማ የአልያንስ ፍራንሴዝ ትምህርት ቤቶች ተቋቁመው ነበር።

 

አጼ ኃይለ ስላሴ በ1923 ዓ.ም ወደ ስልጣን ሲመጡ ዘመናዊ ትምህርትን በሀገሪቷ ውስጥ የማስፋፋት ሥራውን የሚመራ ሀገራዊ የሆነ ተቋም የሥነ-ጥበብ ሚኒስቴር በሚል ስያሜ እንዲቋቋም አድርገዋል። ተቋሙን ለተወሰነ ጊዜ ሀገር ከመምራት በተጨማሪነት ደርበው ከመሩ በኋላ የተቋሙም የመጀመሪያ ሚኒስትር  አድረገው ክቡር ብላቴን ጌታ ሳህሌ ጸዳሉን ሾመዋል። በዚህም መሠረት በወቅቱ በነበረው የአስተዳደር መዋቅር መሠረት በየጠቅላይ ግዛቱ አዳሪ ትምህርት ቤቶች፣ የሴቶች ትምህርት ቤቶች፣ የቴክኒክ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም የሚሲዮንትምህርት ቤቶች እንዲቋቋሙ  ተደርገዋል።

 

ከጣልያን ወረራ በፊት እስከ 1928 ንጉሱ ዳግማዊ ሚኒሊክና ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ 30 ትምህርት ቤቶችን በማቋቋም 5ሺ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲገቡ አድርገዋል፡፡ ተማሪዎቹ ወደ ትምህርት ቤት ገብተው እንዲማሩ ለማድረግ ፍቃደኞችች ባለመሆናቸው በልመና ጭምር እንዲገቡ መደረጋቸውን የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ በወረራው ወቅት ግን እነዚህ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ ተደርገዋል፡፡

 

1928-1933 ዓ.ም ተቋርጦ የነበረው ዘመናዊ ትምህርት ከፋሽስት ጣሊያን ድል መመታት በኋላ በ1934 ዓ.ም አጼ ኃይለ ስላሴ የትምህርት ሥራን በአዲስ መልክ በማንቀሳቀስ የትምህርትና ሥነ-ጥበብ ሚኒስቴርን ዳግም በማቋቋም ክቡር አቶ መኮንን ደስታን ሚኒስትር አድርጎ ሾመዋል። በየጠቅላይ ግዛቱ ተዘግተው የነበሩ ትምህርት ቤቶች እንደገና እንዲከፈቱ የማድረግና ተጨማሪ የማስፋፋት ሥራም ተሠርቷል።

 

ከ1934 እስከ 1966 ከ1ኛ ክፍል ጀምሮ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ወደ 2ሺ የሚጠጉ ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ጠቅላይ ግዛቶች (በወቅቱ አጠራር) ተከፍተዋል፡፡ 14 ኮሌጆች እና 4 የከፍተኛ ትምህርት መስጫ ለዩኒቨርሲቲ መግቢያ የሚያበቁ ተቋሞችም ተከፍተዋል፡፡የካቲት 20/ 1943 በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅን መርቀውም ከፍተዋል፡፡

 

ንጉሱ ከስልጣን ከወረዱ በኋላ ደርግ ሃገር ማስተዳደር ሲጀምር የደርግ መንግሥት የመጀመሪያው የሥነ-ጥበብና ትምህርት ሚኒስትር በመሆን ክቡር አቶ ታደሰ ተረፋ ተሹመዋል። በ1967 ዓ.ም አዲስ አደረጃጀት ተጠንቶ ሥራ ላይ እንዲውል በተደረገው መሠረት ተቋሙ የትምህርትና ሥነ-ጥበብ ሚኒስቴር መባሉ ቀርቶ ትምህርት ሚኒስቴር በሚል ስም መጠራት ጀመረ። በዚህም ሃይለገብርኤል ዳኜ (ዶ/ር) ከ1966-1969 ተረፈ ወልደፃዲቅ (ዶ/ር) ከ1969- 1970፣ ኮለኔል ጎሹ ወልዴ ከ1971-1975፣ አቶ ቢልልኝ ማንደፍሮ ከ1975-1979፣ ያየህይራድ ቅጣው (ዶ/ር) ከ1979-1983 ትምህርት ሚኒስቴርን በሚኒስትርነት መርተዋል። የደርግ መንግስት እስከወደቀበት ጊዜ ድረስ 8ሺ 434 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ 275 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ 17 የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት፣ 2 ዩኒቨርሲቲዎች፣ 3 ኢንስቲቲዩቶችና 5 ኮሌጆች በድምሩ 2ሚሊየን 500ሺ ገደማ ተማሪዎችን ሲያስተምሩ ነበር፡፡

 

በ1983 ዓ.ም ደርግ ከስልጣን ወርዶ የኢህአዴግ ግምባር በሽግግር መንግስት ሀገር መምራት ሲጀምር የኦሮሞ ነፃነት ግምባር ትምህርት ሚኒስቴርን እንዲመራ ተደረገ፡፡ የድርጅቱ ተወካይ አቶ ኢብሳ ጉተማ የሽግግር መንግስቱ የትምህርት ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ፡፡ አቶ ኢብሳ ጉተማ ኦነግ ከሽግግር መንግስቱ ለቅቆ እስኪወጣ ነሃሴ 1984 ዓ.ም ድርስ ትምህርት ሚኒስቴርን በሚኒስትርነት መርተዋል፡፡ በመቀጠል ወ/ሮ ገነት ዘውዴ (በኋላ አምባሳደር) የሽግግር መንግስቱን ቀሪ ጊዜያትና የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ትምህርት ሚኒስትር ሆነው እስከ 1998 ዓ.ም ድረስ መርተዋል፡፡ ስንታየሁ ወልደሚካኤል (ዶ/ር) ከ 1998-2001፣ አቶ ደመቀ መኮንን ከ 2001-2005፣ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ከ2005- 2009፣ ሽፈራው ተክለማሪያም ከ ጥቅምት 2009 እስከ ሃምሌ 2009 ትምህርት ሚኒስቴርን በሚኒስትርነት መርተዋል።

 

የኢህአዴግ ግምባር ድርጅቶች ራሳቸውን አዋህደውና ኢህአዴግ ከስሞ ብልፅግና ፓርቲ ሲመሰረት አዳዲስ የሚኒስቴር መሰሪያ ቤቶች አወቃቀር ማሻሻያ ተደረገ፡፡ በዚህም በ2011 ዓ.ም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ጭምር ይመራ የነበረው ትምህርት ሚኒስቴር ለሁለት ተከፈለ፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ያለውን በመያዝ አጠቃላይ ትምህርትን እንዲመራ ሲደረግ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ስር የነበሩት የአዲስ አበባ እና አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን እንዲመራ "የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር" የሚል አዲስ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ተቋቋመ፡፡ እስከ 12ኛ ክፍል ያለውን አጠቃላይ ትምህርት የሚመራው አዲሱ ትምህርት ሚኒስቴር ሲቋቋም ጥላዬ ጌቴ (ዶ/ር) ታህሳስ 2011 የትምህርት ሚኒስትር ሆነው ተሾመው እስከ 2012 ድረስ ተቋሙን መርተዋል። ከ2012 ጀምሮ ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር ኢንጂ.) ተቋሙን በሚኒስትርነት መርተዋል፡፡

 

በ2013 ዓ.ም መንግስት የአስፈጻሚ መስሪያ ቤቶችን መልሶ የማደራጀት ስራ የተሰራ ሲሆን የትምህርት ሚኒስቴርና የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርን መልሶ በማዋሃድ ቀድሞ ወደነበረበት ትምህርት ሚኒስቴር በሚል ተቋቁሟል። በዚህም መሰረት ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ የትምህርት ሚኒስቴር በመሆን ተሹመው እየሰሩ ይገኛል።