News Detail

National News
Feb 09, 2026 45 views

የዚህ አመት የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና መቶ በመቶ በበይነ መረብ ይሰጣል። በዚህ ዓመት የሚሰጠውን የ2018 የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተና መቶ በመቶ በበይነ መረብ ለመስጠት የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ የግማሽ ዓመት አፈፃፀም መድረክ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት በዚህ ዓመት የሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና መቶ በመቶ በበይነ መረብ እንደሚሰጥ ገልፀዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ፈተናው በወረቀትና በበይነ መረብ ሲሰጥ እንደረበር አንስተው በዚህ ዓመት የሚሰጠውን ማጠናቀቂያ ፈተና ሙሉ በሙሉ በበይነ መረብ ለመስጠት የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ለዚህም የተለያዩ ግብዓቶች ለክልሎች ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው በፈተና ጣቢያዎች በቂ የኢንተርኔት አቅርቦት እንዲኖር ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመነጋገር ይሰራል ብለዋል።
ክልሎች በዚህ ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮች እንዳይኖሩ በቂ ኮምፒዩተር ፣ ኔትዎርክና አማራጭ የሀይል አቅርቦት እንዲኖር ልዩ ትኩረት ሰጥተው መዘጋጀት እንዳለባቸው አሳስበው ለተማሪዎች በቂ ሥልጠና መስጠት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የክልልና ከተማ መስተዳድሮች ይህንን አውቀው አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
እንደ ሀገር ፈተናን በበይነ መረብ ለመስጠት የሚያስችል አቅም መኖሩንና ለዚህም እስካሁን የተሰሩ ሥራዎችን በሚመለከት በትምህርት ሚኒስቴር የዲጅታል ትምህርትና አይሲቲ ሥራ አስፈፃሚ ዘላለም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጻ አድርገዋል።
በገለፃቸውም ተማሪዎች የሚለማመዱባቸው ሞዴል ፈተናዎች በበቂ ሁኔታ የተጋጁ መሆኑን ጠቅሰው ተማሪዎች አስቀድመው እንዲለማመዱና ሥልጠና እንዲያገኙ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
ትምህርት ሚኒስቴር በትምህርት ምዘናና ፈተና አስተዳደር ሥርዓት ውስጥ ያጋጠሙ ስብራቶችን ለማስቀረት የተለያዩ የሪፎርም ተግባራትን ቀርፆ ፈተናን ከስርቆትና ኩረጃ በፀዳ መልኩ ሲሰጥ መቆየቱ ይታወሳል።
Recent News
Follow Us