News Detail
Jul 29, 2025
51 views
የክረምት በጎ ፈቃድ ሥራ የበጎ ተግባራት መገለጫ በተለይም መተጋገዝን፣ መደጋገፍን፣ መረዳዳትንና መከባበር የበለጠ ለማላቅ እድል የሚሰጥ ነው፤ ክብርት ወ/ሮ አየለች እሸቴ፤ የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ የትምህርት ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት አመራሮች በጋምቤላ ክልል ተገኝተው የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎትን አስጀምረዋል።
የትምህርት ሚኒስቴር ፣ ተጠሪ ተቋማት እና የዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ አመራሮች የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎትን በጋምቤላ ክልል ተገኝተው አስጀምረዋል።
በክረምት የበጎ ፍቃድ ማስጀመሪያ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክብርት ወ/ሮ አለሚቱ ኡመድ በሀገራችን ከለውጡ ወዲህ የሀገርን ገጽታ የቀየሩ በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸውን በተለይም የአረንጓዴ አሻራና የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጠቃሽ መሆናቸውን ጠቅሰው ሁለተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ እየተጋች ባለች ሀገር እርስ በርስ መተጋገዝና መደጋገፍ ይገባናል ብለዋል።
አክለውም ትምህርት ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማቱ የዘንድሮ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎትን በጋምቤላ ክልል በማስጀመራቸው ምስጋና አቅርበዋል።
የትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አየለች እሸቴ በበኩላቸው በክቡር ጠቅላይ ሚንስትራችን ሀሳብ አመንጭነት ባልፉት ዓመታት ሲተገብር የቆየው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የበጎ ተግባራት መገለጫ መሆኑን ጠቅሰው በተለይም መተጋገዝን፣ መደጋገፍን፣ መረዳዳትንና መከባበር የበለጠ ለማላቅ እድል የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህ ረገድ ሁሉም ኃላፊነቱን በሚገባ ከተወጣ ኢትዮጵያ የያዘችውን የብልጽግና ጉዞ ለሁሉም እኩል እድል በመስጠት ለማሳካት ትልቅ አቅም ይሆናል ብለዋል።
የትምህርት ሚኒስቴር፣ ተጠሪ ተቋማትና ዩኒቨርሲቲዎች በጋምቤላ ክልል ባስጀመሩት በዚህ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የአቅመ ደካሞችን ቤት ማደስ፣ ችግር ላለባቸው ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግ እና በመትከል ማንሰራራ በሚል ዘንድሮ በተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር የችግኝ ተከላ አካሂደዋል።