News Detail

National News
Mar 05, 2024 1.3K views

ለዲጂታል ትምህርት (e-learning) ተደራሽነትና ጥራት የሚጠቅሙ አምስት የዲጂታል መልቲ ሚዲያ ስቱዲዮዎች ተመረቁ

ለዲጂታል ትምህርት (e-learning) ተደራሽነትና ጥራት የሚጠቅሙ አምስት የዲጂታል መልቲ ሚዲያ ስቱዲዮዎች በአዲስ አበባ፣ በባህርዳር፣ በድሬደዋ፣ በሀዋሳና በጅማ ዩኒቨርሲቲዎች ተመርቀዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር የአስተዳደርና መሠረተ ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ እና የትምህርት ሚኒስትሩ ተወካይ ዶ/ር ሰለሞን አብርሃ የነዚህ ስቱዲዮዎች መገንባት መሰረታዊ ዓላማው ዩኒቨርስቲዎች የተሻሉ ባለሙያዎችን በመጠቀም ጥራቱን እና አግባብነቱን የጠበቀ የኤሌክትሮኒክ ኮርስ ቀረጻ ማካሄድ መሆኑንና ስቱዲዮ የተገነባላቸው ተቋማት በአቅራቢያቸው ለሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የየራሳቸውን ስቱዲዮ እስኪያቋቁሙ ድረስ አገልግሎት መስጠት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡
በዚህ የዲጂታል መርሃ- ግብር የመምህራንን የኤሌክትሮኒክስ ትምህርት አሰጣጥ አቅምን ለመገንባት እና የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ለማስተማር የታቀደ መሆኑን ጠቅሰው በተለይም ለመማር ጊዜ የማይኖራቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ሥራቸው ላይ ምንም ተጽዕኖ ሳይፈጠር ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ዶ/ር ሰለሞን በነዚህ የመልቲ ዲጂታል እስቱዲዮ ግንባታ ሂደት ውስጥ የተሳታፉ አካላትን እስከ አሁን ላበረከቱት አስተዋጽኦ አመስግነው በቀጣይ በሚሠሩ ሥራዎችም ላይ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንድቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡
በአሜሪካ የአሪዞና ስቴት ዩኒቨርሲቲ ተወካይ ዶ/ር ዩካኢ ምላምቦ (Yeukai Mlambo,Ph.D)የተመረቁት መልቲ ሚዲያ ስቱዲዮዎች በዲጂታል ቴክኖሎጂ ረገድ ኢትዮጵያን ወደ ፊት የሚወስዱና በተለይም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጥራት ያላቸውን የማስተማሪያ ግብዓቶችና መሳሪያዎችን በቀላሉ እንዲያገኙ የሚያስችሉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር ዩካኢ ለውጡ ከልማዳዊ የማማር ማስማር ሂደት ወደ ድንበር፣ቦታና ጊዜ የማይገድበው ዲጂታል አለም የተደረገ መሠረታዊ ለውጥ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
ለዲጂታል ስቱዲዮው ከፍተኛ አስተዋጾ ካደረጉት አጋሮች መካከልም የማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ያለው የዚህ ዲጂታል ስቱዲዮ መገንባት የወደፊቱን የተማሪዎችንና የወጣቶቻችንን ሥራ ፈጣሪነት በማጎለበትና ሥራ አጥነትን ከመቀነስ አንፃር ትልቅ ድርሻ ያለዉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳት ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ የተገነቡ ስቱዲዮዎች የትምህርት ተደራሽነትና ጥራትን በማሻሻል በአለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ የሆነ የሰው ሀይል ለማፍራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ መሆኑን ጠቀሰው ስቱዲዮዎቹም እንዲገነቡ ለበረከቱት አስተዋጽኦ ትምህርት ሚኒስቴርን፣የአሪዞና ስቴት ዩኒቨርሲቲንና የማስተር ካርድ ፋውንዴሽንን አመስግነዋል።
የምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተጨማሪ እስቲዲዮ የተገነባላቸው የአራቱ ዩኒቨርሲቲዎች አመራር ከተገነቡ ስቱዲዮዎች በበይነመረብ ለታዳሚዎች መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተገነባው ስቱዲዮም ተጎብኝቷል፡፡