የተቋሙ ስልጣንና ተግባር
የትምህርት ሚንኒስቴር ስልጣንና ተግባር
በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የፌደራል መንግሥት አስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣ አዋጅ ቁጥር 1263/2021 መሰረት ትምህርት ሚኒስቴር የሚከተሉት ስልጣንና ተግባራት ይኖሩታል፣
-
- የአጠቃላይና የከፍተኛ ትምህርት ፖሊሲዎችን፣ ስትራቴጂዎች፣ ሕጎችና እና ፕሮግራሞች ያመነጫል፣ ለአፈጻጸሙ ከሀገራዊ የልማት አቅጣጫ ጋር የተጣጣመ ዝርዝር መርሀ-ግብር ያዘጋጃል፤ በሚመለከተው አካል ሲፀድቅም ተግባራዊ ያደርጋል፤
- የአጠቃላይና የከፍተኛ ትምህርት የሥርዓተ ትምህርት ማዕቀፍ ያዘጋጃል፣ የትምህርት እና የትምህርት ተቋማትን ስታንዳርድ ያወጣል፣ ሀገራዊ የብቃት ማዕቀፍ ያዘጋጃል፣ በሥራ ላይ መዋሉንም ያረጋግጣል፤
- የአጠቃላይና ከፍተኛ ትምህርት ፖሊሲና ሥርዓተ ትምህርት መሠረት ያደረጉ ሀገር አቀፍ ፈተናዎች ዝግጅት፣ ሪከርድ መያዝና የምስክር ወረቀት የመስጠት ሂደቶችን በበላይነት ያስተባብራል፤
- ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በጥናትና ምርምር የጎለበቱ እንዲሆኑ የሚያስችል ስልት ይነድፋል፣ ይተገብራል፤ የጥናትና ምርምር ውጤቶች በሥራ ላይ የሚውሉበትን መንገድ ያመቻቻል፤
- ከኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በከፍተኛ ትምህርትና የምርምር ተቋማት እና በኢንዱስትሪው ዘርፍ መካከል ለምርምርና ቴክኖሎጂ ልማት እንቅስቃሴ የሚያግዝ ምቹ የእርስበርስ ትስስርና ቅንጅታዊ አሠራር እንዲፈጠር ሁኔታዎችን ያመቻቻል፤
- የመንግሥት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን አፈጻጸም ይከታተላል፤
- የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ቅበላና ምደባ አፈጻጸም ፍትሐዊ መሆኑን ያረጋግጣል፤
- የአጠቃላይ እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሊያሟሉ የሚገባቸውን ደረጃ መውጣቱን ያረጋግጣል፤ በተቋማቱ ጥራትና አግባብነት ያለው ትምህርት መሠጠቱን ይከታተላል፤
- ጥራቱን የጠበቀ የከፍተኛ ትምህርት እንዲስፋፋ ያደርጋል፣ በበላይነት ይመራል፤ ትምህርትን በተመለከተ ሀገራዊ የአሕዝቦት ተግባራትን ያከናውናል፣
- በከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁጥር ፩ሺ፩፻፶፪/፪ሺ፲፩ ለከፍተኛ ትምህርት ስትራቴጂክ ማዕከል የተሰጡ ሥልጣንና ተግባራትን ሥራ ላይ ያውላል።