News Detail

የሀገር ውስጥ ዜና
Feb 10, 2026 49 views

የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የተማሪ መጽሃፍትን አንድ ለአንድ ለማድረስ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ፤

ትምህርት ሚኒስቴር ከአጋር አካላት በተገኘ ድጋፍ ያሳተማቸውን 23.9 ሚሊየን የአንደኛ ደረጃ ትምህርት መጽሃፍት ጅቡቲ ወደብ ደርሰው ወደ ሃገር ውስጥ የማጓጓዝ ሥራ እየተሰራ ነው።
ትምህርት ሚኒስቴር በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት መሰረት የተማሪ መጽሃፍትን በሁሉም የትምህርት እርከኖች አንድ ለአንድ ለማድረስ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገልጸዋል።
የአንደኛ ደረጃ ትምህርት መጽሃፍትን ማሟላት የክልል ትምህርት ቢሮዎች ሃላፊነት መሆኑን ያነሱት የትምህርት ሚኒስትሩ ነገር ግን እንደ ሀገር የሚታየውን የተማሪ መጽሃፍት አቅርቦት ችግር ለመፍታት በትምህርት ሚኒስቴር ደረጃ ሀብት በማፈላለግ ከ23.9 ሚሊየን በላይ መጽሃፍትን ማሳተም መቻሉን አብራርተዋል።
እነዚህ የታተሙት መጽሃፍት ጅቡቲ ወደብ ደርሰው የተወሰኑት ወደ ሀገር ውስጥ መግባት መጀመራቸውን ጠቅሰው በመጪዎቹ ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ወደ ሀገር ውስጥ ተጠናቀው በመግባት ለሁሉም ክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች በተቀናጀ ሁኔታ የሚሰራጩ በመሆኑ ክልሎች በፍጥነት በመረከብ ወደ ትምህርት ቤት በማውረድ ተማሪዎቹ መጽሃፍቱን እንዲያገኙ በማድረግ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
እስካሁን በክልሎችና በትምህርት ሚኒስቴር የታተሙት መጽሃፍት በቂ አለመሆናቸውን የገልጹት ሚኒስትሩ በቀጣይ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት መጽህፍትን አንድ ለአንድ ለማደረስ ትምህርት ሚኒስቴር ከተባባሪ አካላት ባገኘው ድጋፍ ተጨማሪ ወደ 40 ሚሊየን የሚጠጋ መጽሃፍትን በድጋሚ አሳትሞ ለክልሎች ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
ትምህርት ሚኒስቴር በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት መሰረት የ2ኛ ደረጃ ትምህርት መጽሃፍትን አሳትሞ ሙሉ በሙሉ ለተማሪዎች አንድ ለአንድ እንዲደርስ ወደ ክልሎች ማሰራጨቱ የሚታወስ ነው።
Recent News
Follow Us