News Detail

National News
Jan 26, 2025 218 views

ስፖርትና እውቀትን በማቀናጀት በትምህርት ጥራት ላይ የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ አስታወቁ።

የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ስፖርት ፌስቲቫል በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ተከፍቷል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ፌስቲቫሉን ሲከፍቱ ባደረጉት ንግግር ስፖርትና እውቀትን ከትምህርት ጥራት ስራዎች ጋር በማስተሳሰር የአገርን እድገት ከፍ ማድረግ ይገባል፡፡
የአእምሮ እድገትና የአካል እድገት የተሳሰሩ መሆናቸውን የጠቆሙት ሚኒስትሩ ተወዳዳሪዎች በቆይታቸው ሰላምን፤ ወዳጅነትና አብሮነትን በማስቀደም የስፖርት ፌስቲቫሎችን ማካሄድ እንደሚጠበቅባቸውም ተናግረዋል።
ከሚቀጥለው የትምህት ዘመን ጀምሮ ዩኒቨርስቲዎችን ጨምሮ በአገር ውስጥ ያሉ ትምህርት ቤቶች በሙሉ አዲስ የሊግ ወድድሮች እንደሚያካሄዱም ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡
በአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ከመጀመሪያ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ያሉ ትምህርት ቤቶች በሊግ ተደራጅተው ከወዲሁ ውድድሮችን በማካሄድ ላይ መሆናቸውንም አመልክተዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ መኪዩ መሐመድ በበኩላቸው የዩቨርስቲዎች ስፖርት ፌስቲቫል በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ስፖርት ማዘውተሪያዎች እንዲስፋፉ ፣ በዩኒቨርስቲዎችና በተማሪዎች መካከል መልካም ግንኙነት እንዲፈጠር፣ የስፖርት ተሳትፎ እንዲጎለብትና ምቹ መማማር ማስተማር ከባቢ እንዲፈጠር እንደሚያስችል ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲዎች ስፖርት ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ አባይ በላይሁን በበኩላቸው ውድድሩ በኮቪድና በተለያዩ ምክንያቶች ለዘጠኝ አመታት ተቋርጦ የቆየውን ውድድር ትምህርት ሚኒስቴር ዩኒቨርስቲዎች ተቀራራቢ ካላንደር እንዲኖራቸው በማድረጉ እውን ሊሆን መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
የውድድሩ አዘጋጅ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ደረጀ እንግዳ በዚሁ ጊዜ ሲናገሩ ስፖርት ለአንድነትና ለእድገት በሚል መሪ ቃል የሚካሄደውን ይህን የስፖርት ፌስቲቫል ቀጣይነት ለማረጋገጥ ዩኒቨርስቲው በአጭር ጊዜ ወስጥ ውድድሩን ማዘጋጀቱን ገልጸዋል።
ከጥር 17 – 27/ 2017 ዓ.ም በሚካሄደው በዚህ ውድድር በአምስት ስፖርት አይነቶች ከ49 ዩኒቨርስቲዎች የተውጣቱ 2500 ስፖርተኞች እንደሚሳተፉ ታውቋል።
Recent News
Follow Us