News Detail

National News
Jan 23, 2025 149 views

በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ወሊሶ ከተማ ለሚገነባው ልዩ አዳሪ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመሰረት ድንጋይ በዛሬው ዕለት ተቀምጧል፡፡

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በኦሮሚያ ክልል ደ/ ምዕራብ ሸዋ ዞን ወሊሶ ከተማ ለሚገነባው ልዩ አደሪ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ በማስጀመር የመሠረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በወቅቱ እንዳሉት ብቁ፣ ተወዳዳሪና ለወደፊት ለሀገሪቱ ጠንካራ መሪ ለማውጣት ግብዓት የተሟላላቸው አዳሪ ትምህርት ቤቶችን መገንባት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ የሚቻለው ጥራት ያለው ትምህርትን ለሁሉም ማድረስ ሲቻል ነው ያሉት ሚኒስትሩ በገጠርም ሆነ በከተማ ሁሉም ዜጋ ጥሩ የትምህርት ዕድል እንዲያገኝም እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የዚህ ትምህርት ቤት ግንባታ በዚህ አመት ተጠናቆ ከመላው ሀገሪቱ ከ8ኛ ክፍል በጣም ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ተመርጠው የሚማሩባት እንደሆነም ገልፀዋል።
በዚህም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ለልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቱ ግንባታ ቦታ በማዘጋጀትና የግንባታ ወጪን መሸፈን ላደረገው ድጋፍም ሚኒስትሩ ምስጋና አቅርበዋል።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ቶላ በሪሶ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት ይህ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ከሌሎቹ ለየት የሚያደርገው ከኦሮሚያ ብቻ ሳይሆን ከመላው ኢትዮጵያ ብቃት ያላቸው ተማሪዎች ተመርጠው የሚማሩበት መሆኑ ነው ብለዋል።
በ1.27 ቢሊየን ብር ወጪ የሚገነባው ይህ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ሙሉ ወጪ በክልሉ መንግስት እንደሚሸፈን ገልፀው ይህም ክልሉ ለትምህርት የሰጠውን ትኩረት ያሳያል ብለዋል።
የልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቱ ግንባታ በዚህ ዓመት ተጠናቅቆ በመስከረም 2018 ዓ.ም የመጀመሪያዎቹን 250 ተማሪዎች ተቀብሎ የማስተማር ሥራውን እንደሚጀመር ጠቁመዋል፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር በትምህርታቸው ብቁና ተወዳዳሪ የሆኑ ተማሪዎች ከመላ ሀገሪቱ ተመርጠው የሚገቡባቸው ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እያስገነባ እንደሚገኝም በመድረኩ ተገልጿል።
የትምህርት ቤቶቹ ግንባታ ሲጠናቀቅም ለመጀመሪያ ጊዜ 1500 የ9ኛ ክፍል ተማሪዎችን ተቀብለው ማስተማር ይጀምራሉ ተብሏል።
Recent News
Follow Us