News Detail
Feb 16, 2026
14 views
በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት መሠረት ለአይነ ስውራን የተዘጋጁ የ2ኛ ደረጃ የብሬል መጽሐፍት እየተጓጓዙ ነው።
የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አየለች እሸቴ በመጀመሪያው ዙር ለስርጭት የተዘጋጁ የብሬል መጽሀፍቱን የስርጭት ሂደት ተመልክተዋል።
ክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ የመጽሐፍቱን ስርጭት ሂደት ምልከታ ባደረጉበት ወቅት እንደገለጹት የትምህርት ጥራት፣አግባብነት ፣ፍትሃዊነትና ተደራሽነትን ለማረጋጥ የተለያዩ የሪፎርም ስራዎች ተግባራዊ እየተደረጉ ይገኛል ብለዋል።
ከሪፎርም ስራዎች መካከልም የተሻሻለውን የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ መነሻ በማድረግ አዲስ ስርዓተ ትምህርት ተቀርጾ ተግባራዊ መደረጉን ክብርት ሚኒስትር ዴኤታ ገልጸዋል።
ተግባራዊ በተደረገው ሥርዓተ ትምህርት መሠረትም ተማሪዎችና መምህራን የሚገለገሉባቸውን የመማሪያና የማስተማሪያ መጽሀፍት አንድ ለአንድ ለማድረስ ሲሰራ መቆየቱንም ክብርት ወ/ሮ አየለች ተናግረዋል።
ሁሉም ዜጎች የመማርና የመማሪያ ግብዓቶችን ማግኘት መብት እንዳላቸው ያስገነዘቡት ክብርት ሚኒስትር ዴኤታ ዜጎች በሁሉም ረገድ እኩል የትምህርት እድል ማግኘት እንዲችሉ እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ለስርጭት የተዘጋጁት የብሬል መጽሐፍት አይስውራን ተማሪዎች በቂ የመማሪያ መጽሐፍት አግኝተው ራሳቸውን በማብቃት ከሌሎች ተማሪዎች ጋር እኩል እድል እንዲያገኙና በእውቀትና በክህሎት ብቁ ሆነው እንዲገኙ እንደሚያስችሉ ገልጸዋል።
የቅድመ አንደኛና የአንደኛ ደረጃ ትምህርት መጽሐፍትን አንድ ለአንድ ለማድረስ ከ 23.9 ሚሊዮን በላይ መጽሐፍት ታትመው እየተሰራጩና እየተጓጓዙ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።
የሥርዓተ ትምህርት ማበልጸጊያ ተጠባባቂ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ዛፉ አብርሃ በበኩላቸው በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ትግበራ ሂደት ለስርጭት የተዘጋጁት የ2ኛ ደረጃ የብሬል መማሪያ ማስተማሪያ መጽሐፍት በስድስት (6) የትምህርት ዓይነቶች የተዘጋጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የብሬል መጽሀፍቱ ለሁሉም ክልል አይነ ስውራን ተማሪዎች መታተማቸውን የገለጹት ወ/ሮ ዛፉ በአሁኑ ወቅት ታትመው የተጠናቀቁት የብሬል መጽሐፍት ከማዕከል ወደ ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ከሰኞ ጀምሮ እንደሚጓጓዙ ጠቁመዋል።
Recent News
የአማሮ ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመረቀ።
Feb 27, 2026
አዲስ የተመደቡ የዩኒቨርስቲ አመራሮች ኃላፊነታቸውን በትክክል እንዲወጡ ተጠየቀ ።
Feb 13, 2026