News Detail
Feb 02, 2022
423 views
ዩኒቨርሲቲዎች በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምህንድስና እና ሂሳብ (STEM) ማዕከላት የሚሰሩ ስራዎችን ተቋማዊ በማድረግ በባለቤትነት ሊመሩ እንደሚገባ ተገለጸ
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሳይንስ፣ቴክኖሎጂ ፣ ምህንድስና፣ ሂሳብ ማእከሎችን በማጠናከር ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሂዷል።
በውይይቱ የተማሪዎች አመራር ስርዓት እና STEM የሚመራበት መመሪያ በውይይት አዳብሮ ወደ ስራ ማስገባት እንደሚገባ ተገልጿል።
የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስቴር ዴኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምህንድስና እና ሂሳብ (STEM) ማዕከላትን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ዩኒቨርሲቲዎች በማዕከላት የሚሰሩ ስራዎችን ተቋማዊ በማድረግ በባለቤትነት ሊመሩ እንደሚገባ ገልፀዋል።
በማዕከላት የሚሰሩ ስራዎችን ተቋማዊ ለማድረግ በመዋቅር እና አሰራር ማስደገፍ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባም ሚኒስቴር ዴኤታው ተናግረዋል።
በመድረኩ የSTEM ማእከላት በዩኒቨርስቲዎች ማቋቋም ተግባራዊ ትምህርት ለማጠናከር እና አካባቢያዊ ችግሮችን የሚፈታ ትውልድ ለመፍጠር ቁልፍ ሚና እንዳለውም ተጠቁሟል።
በቀጣይ አዳዲስ የሚከፈቱ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ምህንድስና ሂሳብ ማእከላትን በሰው ሃይልና በቁሳቁስ ማጠናከር፣ የተማሪዎችና መምህራን መረጃ መያዝ፣ መንግስትና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር ማእከላትን በማጠናከር ዙሪያ የጋራ እቅድ ማውጣት እና መተግበር እንደሚገባም በውይይቱ ተነስቷል።
የዩኒቨርሲቲዎች የSTEM ማእከላት አስተባባሪዎች በበኩላቸው በየማእከላቱ እያጋጠሙ ስላሉ የግብአት፣ የመዋቅር ፣ የሰለጠነ የሰው ሃይል እና ቴክኖሎጂ ችግሮች አንስተው ውይይት አካሄደዋል።
እስካሁን በ33 የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የSTEM ማእከላት ተቋቁመዋል።