News Detail
Nov 23, 2025
31 views
እያደገ የመጣውን ሀገራዊ የዜጎች ፍልሰት ለመቀነስ በምርምር ሥርዓት የሚደገፍ የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራርን አጠናክሮ ማስቀጠል አስፈላጊ መሆኑ ተገለጸ፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር ከዓለም እቀፍ ህጻናት አድን ድርጅት ጋር በመተባበር” በኢትዮጵያ የፍልሰት ምርምርን ለማሳደግ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚና” በሚል መሪ ቃል በፍልሰት ላይ የሚሰሩ የሲቪክ ማህባራት፣መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት የተሳተፉበት አውደ-ጥናት ተካሂዷል፡፡
በአውደ-ጥናቱ መክፈቻ ላይ የተገኙት የትምህርት ሚኒስቴር አማካሪ ሚኒስቴር ዴኤታ ፕሮፌሰር ክንደያ ገ/ህይወት እያደገ የመጣውን ሀገራዊ የዜጎች ፍልሰት ለመቀነስም ሆነ በሚገባ ለማስተዳደር በምርምር ሥርዓት የሚደገፍ የባለድርሻና አጋር አካላት ቅንጅታዊ አሰራርን አጠናክሮ ማስቀጠል አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።
አውደ-ጥናቱ በዩኒቨርሲቲዎች የጋራ ትብብርና ቅንጅት በሚሰሩ ምርምሮች የሚለዩ የህግ ማዕቀፎችና የአተገባበር ክፍተቶች አግባብነት ባላቸው ተቋማት ተወስደው ለአስፈጻሚዎች ውሳኔና ለፋጻሚዎች ትግበራ ማሻሻያነት የሚውሉበት ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር መሆኑን አንስተዋል፡፡
ፕሮፌሰር ክንደያ አክለውም በአሁኑ ወቅት ለፍልሰት በተሰጠው ሀገራዊ ትኩረት የፍልሰት ምርምር ለዩኒቨርሲቲዎች ከተሰጡት የምርምር ስትራጂዎች መካከል አንዱ እንዲሆን ከመደረጉ በተጨማሪ ፍልሰት እንደ አንድ ዋነኛ የማህበረሰብ አጀንዳ ተወሶዶ እንዲሰራበት መደረጉንም ጠቁመዋል።
በዓለም አቀፍ የህጻናት አድን ድርጅት የፕሮግራም ትግበራ ዳይሬክተር አቶ አብዱረዛቅ አህመድ ድርጅታቸው ለብሄራዊ ፍልሰት ምላሽ ድጋፍ ሲሰጥ መቆየቱን ጠቅሰው ከፍልሰት ምርምር የሚገኙ ግብዓቶች ደግሞ ፕሮግራሙ ይበልጥ በውጤታማነት እንዲፈጸም የሚያግዙ እቅዶችን ለማቀድ የሚረዱ በመሆናቸው ድርጅታቸው ምርምርን አጽዕኖት ሰጥቶ የሚደግፍ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ዳይሬክተሩ አክለውም በአሁኑ ወቅት ባሉት የተለያዩ ችግሮች የተነሰ እየጨመሩ የመጡ የፍልሰት ተጋላጭነቶችንና ጉዳቶችን ለመቀንስ ቅንጅትና አስቸኳይ የጋራ ምላሾች የሚያስፈልጉ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በፍትህ ሚኒስቴር ብሄራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ አብረሃም አያሌው ባለፉት ሦስት አመታት ፍልሰት ብሄራዊ የልማትና ደህንነት አጀንዳ ወደ መሆን የተሸጋገረ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ይህም በመሆኑ የተወሰኑ ዩኒቨርሲቲዎች በፍልሰት ላይ ያተኮረ የድህረ-ምረቃ ትምህርት ክፍሎች መክፈታቸውንና የተወሰኑት ደግሞ የፍልሰት ምርምር ማዕከላት ማቋቋማቸውን ገልጸዋል፡፡
ሀገራችን በዓለም አቀፍ፣ በአህጉርና በኢጋድ ሀገራት ደረጃ የተለያዩ የፍልሰት ስምምነቶችን ተቀብላ የህጎቿ አካል አድርጋ እየተገበረች መሆኗን ጠቅሰው ከጥቂት አመታት ወዲህ ለፍልሰት በተሰጠው ትኩረት ሀገራዊ የፍልሰት ረቂቅ ፖሊሲ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡
በአውደ-ጥናቱ ላይ የተላያዩ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት የተካሄደባቸው ሲሆን ለትብብር ጥምረቱ ሴክሬታሪያት ውጤታማነትና ለአውደ-ጥናቱ መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ተቋማትና ግለሰቦች እውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡