News Detail
Dec 05, 2025
53 views
የትምህርት ሚኒስትሩ ከቻይና የመጡ የልዑካን ቡድን አባላትን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ከቻይና የመጡ የልዑካን ቡድን አባላትን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
በዚሁ ጊዜ የልዑካን ቡድኑን የመሩት የቻይና የቋንቋ ትምህርትና ትብብር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር Yu Yunfeng ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር የቆየ ወዳጅነት ያላት ሀገር መሆኗን አንስተዋል።
በተለይም ኢትዮጵያ የቻይና ስትራቴጂክ አጋር ናት ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ በኢንቨስትመንት ረገድ ከምታደርገው ትብብር በተጨማሪ የቻይና ቋንቋ ትምህርት በተወሰኑ ዩኒቨርሲቲዎች እየተሰጠ መሆኑን ጠቅሰው ይህንን በሌሎች የትምህርት ተቋማት በማስፋፋት የቻይና ቋንቋን ማስተማር እንደሚፈልጉ ገልጸውላቸዋል።
ይህም ዜጎች በርካታ ቋንቋዎችን እንዲያውቁ ከማድረጉም ባሻገር የህዝብ ለህዝብ ትብብርን የበለጠ በማጠናከር ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው ኢትዮጵያና ቻይና ለረጅም ጊዜ የቆየ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸውና የብሪክስ አባል ሀገራት መሆናቸውን ጠቅሰው አሁን ባለው የኢትዮጵያና የቻይና ግንኙነት የቻይና ቋንቋ በኢትዮጵያ የትምህርት ተቋማት ቢሰጥ ለዜጎች ጠቃሚ መሆኑን አንስተዋል።
በኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ የቋንቋ ትምህርትን በተመለከተ በግልጽ የተቀመጡ ጉዳዮችን ለልዑካን ቡድኑ ያብራሩት ክቡር ሚኒስትሩ በተወሰኑ ዩኒቨርሲቲዎች የተጀመረውን የቻይና ቋንቋ ትምህርት በሌሎች የትምህርት ተቋማት ለማስፋፋት ፍላጎቶች እንዳሉና አተገባበሩን በተመለከተ ውይይት ማድረግ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
አያይዘውም በዚህ ዓመት የመማር ማስተማር በሚጀመርባቸው አምስት የፌዴራል ልዩ አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የቻይና ቋንቋን ለማስተማር በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ፍላጎት እንዳለ በማንሳት የቻይና ቋንቋ መምህራንን እንዲመደቡ የልዑካን ቡድኑን ጠይቀዋል።
ሁለቱ አካላት በውይይታቸውም በፌዴራል ልዩ አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚሰጠውን የቻይና ቋንቋ ትምህርትን በተመለከተ የሥርዓተ ትምህርት ማዕቀፍ መዘጋጀት እንዳለበት እና በሌሎች የትምህርት ተቋማት ለመተግበር እንዲቻል የሥርዓተ ትምህርት፣ የመጽሃፍት እና የመምህራን አቅርቦትን በተመለከተ አስቀድሞ መወያየት እንደሚገባ አንስተዋል።
በመጨረሻም በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ ስምምነት የተደረሰባቸውን ጉዳዮች ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ዝርዝር የስምምነት ሰነድ ከሁለቱ አካላት በተውጣጣ ኮሚቴ እንዲዘጋጅ ከስምምነት ላይ ተደርሷል።