News Detail
May 20, 2025
14 views
በኢትዮጵያና በአውሮፓ ህብረት ሀገራት የትምህርትና ስልጠና ተቋማት ጋር ያለውን የትብብር ግንኙነት ማጠናከር እንደሚገባ ተመላከተ፤ የአውሮፓ ህብረት የኢራስመስ (ERASMUS +) ትብብር የተዘጋጀ ጉባዔ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል በጉባኤው መክፈቻ ላይ እንደገለጹት በኢትዮጵያ እና በአውሮፓ ህብረት መካከል ያለውን የትምህርትና ስልጠና አጋርነት ጥራትና ተገቢነቱን በማሳደግ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል።
በትምህርትና ስልጠና ተቋማት መካከል ግንኙነት በማጠናከር ውጤታማ የልማት ትብብሮችን መተግበር እንደሚገባም ወ/ሮ ሙፈሪሃት አስገንዝበዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር የአካዳሚክ ጉዳዮች መሪ ሥራ አስፈጻሚና የብሔራዊ ኢራስመስ (ERASMUS +) ተወካይ ኤባ ሚጀና (ዶ/ር) በበኩላቸው በኢራስመስ የትምህርትና ስልጠና ድጋፍ እኤአ ከ2010 እስከ አሁን ድረስ ከ600 በላይ ኢትዮጵያውያን ነጻ የትምህርት እድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ዛሬ የተጀመረው የአውሮፓ ህብረት የኢራስመስ የትምህርትና ስልጠና ድጋፍና ትብብር ጉባኤ ዓላማ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሃራ በታች ላሉ የአፍሪካ አገራት ያለውን የትምህርትና ስልጠና ግንኙነት ተጠናክሮ በሚቀጥልበት ሁኔታ ለመምከር መሆኑንም ዶ/ር ኤባ ጨምረው ገልጸዋል።
በአውሮፓ ህብረት የትብብርና አለማቀፋዊነት ልዑክ ሃላፊ ሚስተር ሮቤርቶ ሺሊሮ በበኩላቸው ኢራስመስ (ERASMUS) በትምህርት፣ በስልጠና ፣በወጣቶች በስፖርትና በባህል ላይ አትኩሮ የሚሰራ) የአውሮፓ ህብረት ፕሮግራም መሆኑን አስረድተዋል።
" የትምህርት ሚና በአረንጓዴ ሽግግር" በሚል ርዕስ ዛሬ የተከፈተው ይሄው ጉባኤ እስከ ረቡዕ ግንቦት 14/2017 ዓ.ም የሚቀጥል ሲሆን በጉባኤው ላይ 46 ሀገራት (13 ከአውሮፓ ህብረት ሀገራት፣ 32 ከሰሃራ በታች ካሉ ሀገራት እና 1 ሰሜን አፍሪካ) የተወከሉ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።