News Detail
Apr 28, 2025
4 views
በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት Innovation Africa 2025 ጉባኤ መካሄድ ጀምሯል። የትምህርት፣የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂና የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ከ’ African Brains’ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት Innovation Africa 2025 ጉባኤ በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል መካሄድ ጀምሯል።
በዚህ Innovation Africa 2025 የትምህርት፣ የቴክኖሎጂና ክህሎት ጉባኤ ላይ የአፍሪካ ሀገራት የዘርፉ ሚኒስትሮችና ልዑካን ቡድን አባላት፣ የተለያዩ ዓለም አቀፍ የትምህርት አጋር ድርጅቶች፣ የግሉ ሴክተር ኢንቨስተሮች እየተሳተፉ ይገኛል።
ጉባኤውን በንግግር የከፈቱት የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ቀጣዩን ትውልድ ለመገንባት ትምህርት፣ ቴክኖሎጂና ክህሎት በጣም መሳኝ በመሆናቸው በዚህ ጉባኤ ትርጉም ያለውና የሚተገበር ውይይት እንደሚደረግ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ትምህርትና ክህሎትን ማዕከል በማድረግ በትምህርት ቤት ግንባታና መሠረተ ልማት ማሻሻል፣ በድጂታል ኔትዎርክ ግንባታ እንዲሁም በፈጠራና ክህሎት ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝም አንስተዋል።
እንደ አፍሪካ በዚህ ረገድ የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት እጅ ለእጅ ተያይዘን በጋራ እንስራ ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው አሁን ያለንበት የአለም ሁኔታ በጣም የተወሳሰበ በመሆኑ መጪውን ትውልድና ወጣት በትምህርት፣ በቴክኖሎጂና በክህሎት ማዘጋጀት ይጠበቃል ብለዋል።
በመሆኑም ይህ በሦስት ቀን በትምህርት፣በቴኖሎጂና በክህሎት ዘርፍ የምናደርገው ውይይት በትክክል ለአፍሪካ ለውጥ መሠረት የሚጣልበት ሊሆን ይገባል ብለዋል።
በጉባዔውም ከትምህርት፣ አይሲቲ እና ከክህሎት ጋር የተያያዙ ወሳኝ አጀንዳዎች ቀርበው ውይይት የሚደረግባቸው ይሆናል።