News Detail
Jun 27, 2024
589 views
2ኛው አመታዊ አገር አቀፍ የፍልሰት ጥናትና ምርምር ጉባኤ ተካሄደ
2ኛው አመታዊ አገር አቀፍ የፍልሰት ጥናትና ምርምር ጉባኤ በትምህርት ሚኒስቴር፤ በፍትህ ሚኒስቴር፣ በጀርመን ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት እና በሴቭ ዘ ችልድረን አስተባባሪነት ተካሄዷል።
የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በላይሁን ይርጋ በጉባኤው መክፈቻ ላይ ባስተላለፉት መልእክት የተቀናጀና የተሻለ የፍልሰት አስተዳደር ሥርዓት ለመዘርጋት የፖሊሲ ግብዓት የሚያቀርብ በትምህርት ሚኒስቴር የሚመራ የፍልሰት ጥናትና ምርምር ቡድን ተቋቁሞ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የጉባኤውም የተሽላ የፍልሰት አስተዳደር በመፍጠር ኢ-መደበኛ ፍልሰትን ለመቆጣጠርና መደበኛ ፍልሰትን ለማበረታታት የሚያስችል የፖሊሲ ግብዓት ለማሰባሰብ የሚያግዝ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በትምህርት ሚኒስቴር የምርምርና ስርጸት ዴስክ ሃላፊ ዶ/ር ሠራዊት ሃንዲሶ በትምህርት ሚኒስቴር የሚመራው የፍልሰት ጥናትና ምርምር ቡድን በሰዎች የመነገድ፣ ድንበር የማሻገር ወንጀሎችን መከላከል፤ ከስደት ተመላሾችን መልሶ ማቋቋም የሚያስችሉ የፖሊሲ ግብዓቶችን እያቀረበ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ኢ-መደበኛ ፍልሰትን መከላከል የሚያስችል ጥልቅ ጥናትና ምርምር በማከናወን የተቀናጀ የፍልሰት አስተዳደር ሥርዓት ለመዘርጋት እየተሠራ መሆኑን ጥቅሰው የፍልሰት ጥናትና ምርምር ቡድን በተለይ ከስደት ተመላሾች ላይ ትኩረት በማድረግ "የት፤ ምን ተጠና" የሚለውን በመለየት የጥናት ውጤቶችን ለፖሊሲ አውጪዎችና ውሳኔ ሰጪዎች ግብዓት እንዲሆኑ እያቀረበ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
በጉባኤው በኢትዮጵያ 29 ፍልሰት የሚበዛባቸው ዞኖች፣ 14 የድንበር መውጫ በሮች፣ 135 መተላለፊያ ቦታዎች መኖራቸው ተመላክቷል፡፡
በመድረኩም ከ2010 ዓ.ም ወዲህ በተለያዩ ሀገራት በችግር ላይ የነበሩ 500 ሺህ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው መመለስ መቻሉን እና በተያዘው የ2016 በጀት ዓመት ብቻ ከ300 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት እድል መሰጠቱ ተነስቷል፡፡
በጉባኤው ከጥናትና ምርምሮች በተጨማሪ ከፍልሰት ጋር ተያያዥነት ያላቸው የፍትህ ሚኒቴር፣የሴቶችና ማህባራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የእቅድ አፈጻጸሞች ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡
Recent News
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የምግብ ሜኑ ተመሳሳይ እንዲሆን ተወሰነ።
Dec 09, 2024
የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክህሎትን ለማሳደግ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተጠቆመ።
Dec 07, 2024