News Detail

National News
Apr 04, 2024 814 views

የትምህርት ሚንስትሩ ክቡር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደርን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ።

የትምህርት ሚንስትሩ ክቡር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በኢትዮጵያ የጃፓን ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደርን Shibata Hironori በጽ/ቤታቸው ተቀብለው ውይይት ያደረጉ ሲሆን በውይይታቸውም በሁለቱ ሀገራት የትምህርት ዘርፍ ትብብር ዙሪያ በጋራ ለመስራት ስምምነት አድርገዋል።
ክቡር አምባሳደር Shibata Hironori ሀገራቸው አንጋፋውን የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ለማገዝና ከጃፓን ዩኒቨርስቲዎች ጋር ለማስተሳሰር እንደሚሰሩ ገልጸዋል። ክቡር አምባሳደሩ አክለውም ዩኒቨርስቲው ኦቶኖመስ ለመሆን የሚያደርገውን ሂደት ለመደገፍና ከዩኒቨርስቲው ጋር በምርምር ስራዎች ዙሪያ በጋራ ለመስራት፣ ፕሮፌሰሮች የሚያደርጉትን የልምድ ልውውጥ ለመደገፍ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።
በተጨማሪም በሁለቱ ወገኖች ውይይት የጃፓን አለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (JICA) አራት (4) የሚሆኑ የአንደኛ ደረጃ ት/ቤቶችን በአዲሲቷ ኢትዮጵያ የት/ቤቶች ዲዛይን መሰረት ገንብቶ ለማስረከብ ስምምነት ተደርጓል።
እንደ ክቡር አምባሳደሩ ገለጻ ሀገራቸው የሁለቱን እህትማማች ሀገራት ግንኙነት ለማጠናከር ሀያ (20) የሚሆኑ በሂሳብና በሳይንስ ትምህርቶች ላይ የሚሰሩ ጃፓናውያን በጎ ፈቃደኞች እንደምትልክ ቃል ገብተዋል።
በመጨረሻም ለስምምነቱ ተግባራዊነት ሁለቱም ወገኖች በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ገልጸው ውይይታቸውን አጠናቀዋል።