News Detail

National News
Apr 14, 2024 1.1K views

የማንበብ ፣ የመጻፍና የማስላት ክህሎትን በአንድ ዓመት ውስጥ ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው

የትምህርት ሚኒስቴር የኩባ ሊትሬሲ ሞዴልን በመጠቀም ዜጎች በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የማንበብ ፣ የመጻፍና የማስላት ክህሎትን እንዲያሳድጉ እያደረገ ነው። ይህንን አሰራር ወደ ሁሉም ክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች በማውረድ ተግባራዊ እንዲሆን እያተደረገ ሲሆን ክልሎችም በንቃት እየሰሩበት ይገኛሉ።
ከዚህ አንጻር በሲዳማ ክልል የጎልማሶችን የማንበብ፣ የመጻፍ እና የማስላት ክህሎት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቋል።
በክልሉ ከ75ሺ የሚበልጡ ጎልማሶች መሠረታዊ የጎልማሶች ትምህርት በመከታተል ላይ እንደሚገኙ ተጠቁሟል፡።
የሲዳማ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል የቢሮ ኃላፊና የመማር ማስተማርና ምዘና ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታፈሠ ገ/ ማርያም እንደገለጹት በክልሉ በተለያዩ ምክንያቶች የመማር እድል ያላገኙና ከትምህርት ገበታ ውጪ የሆኑ ጎልማሶችና ወጣቶችን ወደ ትምህርት ቤት ለማምጣት እየተሰራ ነው፡፡
በክልሉ ከትምህርት ገበታ ውጪ የሆኑ ጎልማሶችና ወጣቶችን ወደ ትምህርት ቤት ለማምጣትም በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የጎልማሶች ትምህርት መስጫ ጣቢያዎች እንዲከፈቱ እና ትምህርት ቤቶች የጎልማሶችን ትምህርት በኃላፊነት እንዲያስተባብሩና እንዲከታተሉ እየተደረገ መሆኑን አቶ ታፈሠ ገልጸዋል፡፡
በዚህም በክልሉ ሁሉም ወረዳዎች በ1 ሸህ 320 የጎልማሶች ትምህርት ጣቢያዎች 1 ሺህ 461 አመቻቾች በመደበኛ ቅጥር ፣ በኮንትራትና በበጎ ፈቃድ እንዲሟሉና 412 ርዕሳነ መምህራንም ተመድበው ጎልማሶችን በማስተማር ላይ መሆናቸውን ምክትል ቢሮ ኃላፊው አቶ ታፈሠ አስረድተዋል።
በአሁኑ ጊዜ በክልሉ ሰላሳ ሰባት ወረዳዎች 87 ሺ 753 ጎልማሶችን ለማስተማር ታቅዶ 75ሺ 443 ጎልማሶች ተመዝግበው መሰረታዊ የጎልማሶች ትምህርት በመከታተል ላይ መሆናቸውንም ምክትል የቢሮ ኃላፊው ጨምረው ገልጸው ይሄው ፕሮግራም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
የክልሉ ትምህርት ቢሮ የጎልማሶችና መደበኛ ያልሆነ ትምህርት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተሻለ ሸለመ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም ሁለት ዓመት የነበረው መሰረታዊ የጎልማሶች ትምህርት ፕሮግራም እንደ ክልሉ ተጨባጭ ሁኔታ በአንድ ዓመት እንዲጠናቀቅ እየተሰራ ነው ብለዋል።።
መርሀ ግብሩ ቀደም ሲል የተቀናጀ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት ይባል እንደነበር ገልጸው መሰረታዊ የጎልማሶች ትምህርት በመሆን ከስያሜው ጀምሮ በአሁኑ ጊዜ ለውጥ ተደርጎበት ጎልማሶችን በአንድ ዓመት የመጻፍ ፣ የማንበብ እና የማስላት ክህሎትን ማስቻል ትኩረት ያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡።
በክልሉ የመሰረታዊ ጎልማሶች ትምህርት ከትምህርት ቤቶች በተጨማሪ በቤተ እምነቶች፣ በአርሶ አደር ማሰልጠኛ ጣቢያዎች፣ በግል ተቋማት እንዲሁም በማረሚያ ቤቶች ጭምር በመርሀ ግብሩ የሚማማሩ ጎልማሶች መኖራቸውንም ዳይሬክተሩ አቶ ተሻለ አመልክተዋል።።
የዳራ ወረዳ ትምህርት ጽ/ ቤት ኃላፊ አቶ ተመስገን ታደሰ እና የዳራ አትልቾ ወረዳ ትምህርት ጽ/ ቤት ኃላፊ አቶ ታምሩ ላሚሶ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት መሰረታዊ የጎልማሶች ትምህርት በወረዳዎቻቸው በሚገኙ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ቅጥር ግቢዎችና ከቅጥር ግቢ ውጪ በተቋቋሙ የጎልማሶች ትምህርት መስጫ ጣቢያዎች ትምህርት በመከታተል ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በወረዳዎቹ በጎልማሶች ፍላጎትና ምርጫ በሳምንት ሁለት ቀናት ለሶስት ሰዓታት እየተሰጠ የሚገኘውን መሰረታዊ የጎልማሶች ትምህርት በሁሉም የመማማሪያ ጣቢያዎች ተጠናክሮ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
Recent News
Follow Us