News Detail

National News
Apr 16, 2024 1.2K views

ሁሉም ባለድርሻና አጋር አካላት ለጎልማሶች መሰረታዊ ትምህርት ፕሮግራም ስኬታማነት የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተጠየቀ፡፡

በኦሮሚያ ብ/ክ/መ/በአርሲ ዞን የሌሙና ብልብሎ ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ጫላ አበራ የቢልቢሎ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት የጎልማሶች መማሪያ ማዕከልን ባስጎበኙበት ወቅት የህዝባችንን እኩል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥም ሆነ የሀገራችንን እድገት ለማፋጠን ሁሉም ባለድርሻና አጋር አካላት ለጎልማሶች መሰረታዊ ትምህርት ፕሮግራም ስኬታማነት የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባቸው ጠይቀዋል፡፡
አቶ ጫላ ለፕሮግራሙ ስኬታማነት የወረዳው ትምህርት ጽ/ቤት መማር የሚጠበቅባቸውን ጎልማሶች ለይቶ በማወቅ አሳምኖ ወደ ስልጠና ማዕከሉ በማምጣትም ሆነ በመማር ማስተማር ሂደቱም ላይ ቀጣይነት ያለው ድጋፍና ክትትል እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አቶ ጫላ አክለውም በያዝነው በ2016 ዓ.ም በወረዳው 4,623 ጎልማሶች በ60 የማስተማሪያ ማዕከላት ውስጥ በመማር ላይ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡
የብልብሎ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ጥበቡ አንበሴ ለጎልማሶች መማሪያ ማዕከሉ ከመደበኛው ትምህርት እኩል ትኩረት ሰጥተው እያስተዳደሩ መሆኑን ጠቁመው ይህ መሆኑ ለፕሮግራሙ ስኬታማነት አስተዋጽኦ እንደነበረው ገልጸዋል፡፡
የማዕከሉ አመቻች መምህርት ስኳሬ ድሪባ ለፕሮግራሙ በተዘጋጀው መመሪያ መሰረት የአንድ አመት ትምህርታቸውን በውጤታማነት ያጠናቀቁ ጎልማሶች በመደበኛው ትምህርት 3ኛ ክፍል ገብተው ትምህርታቸውን መቀጠል የሚችሉ መሆኑን ጠቁመው ይህንን መብታቸውን ለመጠቀም ጥቂት የማይባሉ ጎልማሶች ከወዲሁ ከአፋን ኦሮሞ በተጨማሪ የእንግሊዝኛ ቋንቋ መሰረታዊ ትምህርትም እንዲሰጣቸው መጠየቅ መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡
Recent News
Follow Us