News Detail

National News
Apr 16, 2024 1.1K views

መሠረታዊ የጎልማሶች ትምህርት በመደበኛ ት/ቤቶች የትምህርት መጠነ-ማቋረጥን እንዲቀንስ ማድረጉ ተገለጸ

ሲዳማ ብ/ክ/መንግስት ትምህርት ቢሮ የጎልማሶችና መደበኛ ያልሆኑ ትምህርቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተሻለ ሸለመ እንደገለጹት በክልሉ ተግባራዊ የተደረገው መሰረታዊ የጎልማሶች ትምህርት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የመጠን መቋረጥ ፣ ማርፈድና ከትምህርት ገበታ መቅረት እንዲቀንስ አስችሏል፡፡
እንደ ሃላፊው ገለጻ በትምህርት ቤቶች መጠነ - ማቋረጥ የቀነሰው በክልሉ ሰላሳ ሰባት ወረዳዎች መሰረታዊ የጎልማሶች ትምህርት ጣቢያዎች ትምህርት የሚከታተሉ ጎልማሶችና ወላጆች የትምህርትን ጠቀሜታ በመገንዘብ ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤቶች በመላካቸውና አስፈላጊውን ክትትል ማድረግ በመጀመራቸው ነው።
በክልሉ መሰረታዊ የጎልማሶች ትምህርት ተግባራዊ መደረግ ከጀመረ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ማንበብ ፣ መጻፍና ማስላት የማይችሉ ጎልማሶች ማንበብና መጻፍ እንዲሁም መሰረታዊ የሂሳብ ስሎቶችን ማስላት መቻላቸውንም የጎልማሶችና መደበኛ ያልሆነ ትምህርት ዳይሬክተሩ አመልክተዋል።
ጎልማሶቹ ከስራቸውና ከእለት ተለት የኑሮ እንቅስቃሴዎቻቸው ጋር የተዛመዱ ትምህርቶችን በመማራቸው በቁጠባ ፣ በማዳበሪያና ምርጥ ዘር አጠቃቀም፣ በኮምፖስት ዝግጅት ፣ በዶሮ እርባታና በሌሎችም በእርሻና እንስሳት ልማት ስራዎቻቸው ውጤታማና ምርታማ መሆናቸውን አቶ ተሻለ ተናግረዋል፡፡
የዳራ ኦቲልቾ ወረዳ ትምህርት ጽ/ ቤት ኃላፊ አቶ ታምሩ ላሜሶ እና የዳራ ወረዳ ት/ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተመስገን ታደሰ በበኩላቸው በወረዳው የጎልማሶች ትምህርት ማዕከላት መሰረታዊ ትምህርት የሚከታተሉ ጎልማሶች ማንበብ ፣ መጻፍና ማስላት ብቻ ሳይሆን በኑሯቸውም ለውጥ እያመጡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በክልሉ በ2016 የትምህርት ዘመን በክልሉ ሁሉም ወረዳዎች 75ሺ 443 ጎልማሶች በ 1ሺህ 320 የጎልማሶች ትምህርት ጣቢያዎች ተመዝግበው በመማር ላይ እንደሚገኙ ከክልሉ ትምህርት ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
Recent News
Follow Us