News Detail

National News
Jun 24, 2025 13 views

አገር አቀፍ የቅድመ ልጅነት ዕድገትና ትምህርት ንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተካሄደ።

በንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ ባለፉት ሁለት አመታት በመንግስትና በማህበረሰቡ በተሰሩ ስራዎች የቅድመ አንደኛ ትምህርትን በማስፋፋትና ተደራሽ በማድረግ ረገድ ስኬቶች እየተመዘገቡ መሆኑ ተገልጿል።
"ልጆቻችን ብሩህ ነገን እንዲፈጥሩ መሠረቱን ዛሬ እንጣል " በሚል በተከናወነው መርሃ ግብር ላይ የትምህርት ሚኒስቴርና የሌሎች ባለድርሻ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ቁልፍ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚንስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በመርሃ ግብሩ መክፈቻ ላይ ባስተላለፉት ቁልፍ መልዕክት የቅድመ ልጅነት እድገትና ትምህርት ላይ የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት በመስጠት ሊሠራበት የሚገባው ጉዳይ መሆኑን የገለጹ ሲሆን አሁን ላይ ከሚመለከታቸው ሴክተር መስሪያ ቤቶችና የልማት አጋሮች ጋር በተፈጠረው ቅንጅታዊ አሰራር አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን ጠቁመዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚንስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አየለች እሸቴ በበኩላቸው ባስተላለፉት ቁልፍ መልዕክት የትምህርት ጥራትን በማጐልበት የሀገርን ብልጽልግና በማረጋገጥና ዜጎች ከሚመዘገበው ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ ትምህርት ቁልፍ ሚና ያለው መሆኑን በመግለጽ የቅድመ ልጅነት እድገትና ትምህርት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት በትምህርትና ስልጠና ፖሊሲውና በአጠቃላይ ትምህርት አዋጁ በተገቢው ሁኔታ እንዲካተት መደረጉን ያስገነዘቡት ሚንስትር ዴኤታዋ ህፃናት ጥራት ያለው የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ማግኘታቸው የትምህርት ስርዓታችን ለገጠመው ስብራት መሰረታዊና ዘላቂ ለውጥ የሚያመጣ መሆኑን አብራርተዋል።
በዘርፉ ላይ ጠንካራ መሰረት ከተጣለ ሀገር የምትፈልገውን ዜጋ ለመቅረጽና ብሩህ የወደፊት ራዕይ ያላው ትውልድ ለመገንባትና ለማፍራት ብሎም የተጀመረውን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ የትምህርት ዘርፉ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስችለው መሆኑን አያይዘው ገልጸዋል።
የጤና ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ እንደዚሁ በተመሳሳይ የትምህርት ዘርፉ ለቅድመ ልጅነት እድገትና ትምህርት የተሰጠው ትኩረት የነገዋን ኢትዮጵያ እጣ ፋንታ የሚወስን በመሆኑ የጤና ሚኒስቴር ድጋፍና ትብብር ሁሌም የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ቤት መሻሻል መሪ ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ዬሀንስ ወጋሶ በበኩላቸው ባቀረቡት ገለጻ በቅድመ ልጅነት ትምህርት ዘርፍ ቀደም ሲል የነበሩ ጉድለቶችና ክፍተቶች ዛሬ ላይ ለሚስተዋለው የተማሪዎች የትምህርት አቀባበልና ውጤታማነት ላይ አሉታዊ ተጽኖ ያለው በመሆኑ ችግሩን ከስር መሠረቱ ለመፍታት በቁርጠኝነት እየተሠራ መሆኑን አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ምክትል ተወካይ ማሪኮ ካጎሺማ በበኩላቸው በዘርፉ የሚከናወኑ ስራዎችን ዩኒሴፍ እንደሚደግፍ ገልጸዋል።
የቅደመ አንደኛ ደረጃ ትምህርትን ለማስፋፋትና በተሻለ ተደራሽ ለማድረግ የትምህርት ሚኒስቴር ከክልልና ከተማ መስተዳድር ትምህርት ቢሮዎች ጋር የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ተፈራርሟል።
Recent News
Follow Us