News Detail
Nov 21, 2022
3.5K views
"የከፍተኛ ትምህርት የለውጥ ተግባራት የትምህርት ጥራት ለማስጠበቅ መሠረት የሚጥሉ ናቸዉ " ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ የት/ት ሚኒስትር ዴኤታ
ህዳር 8/2015ዓም (ትምህርትን ሚኒስቴር) በከፍተኛ ትምህርቱ ዘርፍ የተከናወኑ እና በመከናወን ላይ ያሉ ተግባራትና ያጋጠሙ ችግሮችን አስመልክቶ የ31ኛው ሀገር አቀፍ ትምህርት ጉባኤ ቅድመ -ጉባኤ ምክክር በሃዋሣ ዩኒቨርስቲ እየተካሄደ ነው።
2014 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የተከናወኑ እና አሁን በመከናወን ላይ ያሉ የለውጥና ልማት ስራዎች ሪፓርት እና የ2015ዓም እቅድ በከፍተኛ ት/ት ልማት ዘርፍ መሪ ስራ አስፈፃሚዎች ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
ምክክሩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ራስ ገዝ የማድረግ ሂደቶች ፣የከፍተኛ ትምህርት አለማቀፋዊነት፣ የመውጫ ፈተና ፣የአስተዳደርና ልማት ጉዳዮች እንዲሁም ሌሎች ቁልፍ ጉዳዮች የተዳሠሡበት ነው።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ራስ ገዝ በማድረግ ሂደት ውስጥ ተቋማት ያላቸውን አካባቢያዊ ፀጋ እና ሌሎች አቅሞችን ለመጠቀም የሚያስችላቸውን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት በማስገባት መንቀሳቀስ እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።
የከፍተኛ ትምህርት አለማቀፋዊነትን ከማስፋትና ተወዳዳሪነትን ከማሣደግ አንጻር ተቋማት ጊዜውን የዋጀ የሀብት አጠቃቀም ሥርአት እንዲዘረጉና ተግባራዊ እንዲያደርጉ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ሚንስትር ዴኤታ አሳስበዋል።
በምክክር መድረኩ ቁልፍ የለውጥ አጀንዳዎች ተነስተው ከዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንቶች ፣ከተጠሪ ተቋማት ስራ ሀላፊዎች፣ከመምህራን ማህበርና ሌሎች ባለድርሻ ተቋማት የስራ አመራሮች ጋር ውይይቱ እንደቀጠለ ነው።
የቅድመ ጉባኤ መድረኩን እንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት በማስተላለፍ የሃዋሳ ዩኒቨርስቲ ፕ/ት ዶ/ር አያኖ ባራሶ ከፍተዋል።
በነገው እለት በሚካሄደው 31ኛው ሀገር አቀፍ የትምህርት ጉባኤ ዛሬ በትይዩ የተደረጉ መድረኮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ጨምሮ ከ400 በላይ ተሳታፊዎች ይሳተፋሉ።