News Detail
Nov 21, 2022
3.2K views
የትምህርት ዘርፉ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ የነበረ ቢሆንም በርካታ ውጤቶች የተመዘገቡበት እንደነበር ተገለፀ።
በትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ፋንታ ማንደፍሮ (ዶ/ር) የትምህርት ዘርፉ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ፈተናዎችን ያስተናገደ ቢሆንም በሁሉም አካላት የጋራ ጥረት በርካታ ውጤቶች የተመዘገቡበት እንደነበር ገልፀዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው በ31ኛው ሀገር አቀፍ የትምህርት ጉባዔ ቅድመ ጉባኤ ጎናዊ የዘርፎች ውይይት መድረክ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ባለፉት ሁለት ዓመታት በርካታ መምህራንና ተማሪዎች ከቄያቸው የተፈናቀሉበትና ከትምህርት ገበታ ውጪ የሆኑበት እንዲሁም በርካታ የትምህርት ተቋማት የወደሙበት ዓመት በመሆኑ በነዚህ አካባቢዎች ትምህርት ለማስጀመር ከባድ ፈተና ሆኖ መቆየቱን ጠቁመዋል።
አሁን ላይ በጦርነቱ የወደሙ የትምህርት ተቋማትን መልሶ ለመገንባት የሀብት ማፈላለግ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው ልዩ አዳሪና ሞዴል ትምህርት ቤቶችን በሁሉም ክልሎች ለመገንባት የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን አብራርተዋል ።
የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተና በዩኒቨርስቲዎች ለመስጠት በነበረው ሂደት ከፈተና ዝግጅት ፣ህትመት፣ ስርጭት እንዲሁም ፈተና እስከ መስጠት የነበሩ ችግሮችን ፈትቶ በስኬት ማጠናቀቅ መቻሉን ሚኒስትር ዴዔታው አብራርተዋል ።
በአዲሱ ዓመት አዲሱ ስርዓተ ትምህርት ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ወደ ሙሉ ትግበራ ከ9ኛ እስከ 10ኛ ክፍል ደግሞ ወደ ሙከራ ትግበራ መገባቱ በመድረኩ ተገልጿል ።
በጉባኤው ላይ የሲዳማ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድር እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በየነ ብራሳ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በጉባኤው ላይ የሁሉም ክልልና ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮዎች፣ የፓርላማ አባላትና ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን ጉባኤው ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ ሦስት ቀናት የሚካሄድ መሆኑም ታውቋል።