News Detail
ትምህርት ዘርፍ አመራሮች ፣ሠራተኞችና የግል ኮሌጆች ለአገር መከላከያ ሚኒስቴር ከ29 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብና የዓይነት ድጋፍ አደረገ።
የትምህርት ሚኒስቴር ደኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት እንዳሉት ትምህርት ሚኒስቴርና ሁለቱ ተጠሪ ተቋማቱ ድጋፉ.ን ያደረጉት በጀግናው የአገር መከላከያ ሰራዊት እየተከፈለ ላለው ዋጋ እውቅና ለመስጠት ነው።
ከቅርብም ከውጪም ጥቅማቸው የተነካባቸው ኃይሎች በአገራችን ላይ የከፈቱትን ጥቃት በመመከት ላይ ለሚገኘው ጀግናው የአገር መከላከያ ሰራዊታችን ትምህርት ሚኒስቴር እያደረገው ያለው ድጋፍ ለወደፊቱም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ድጋፉን የተረከቡት የመከላከያ ሚኒስቴር ደኤታ ወ/ሮ ማርታ ሉዊጅ በበኩላቸው የትምህርት ሚኒስቴር ላደረገው የገንዘብና የዓይነት ድጋፍ አመስግነው ሠራተኞቹ በሞራል፣ በገንዘብ ፣ በቁሳቁስና በደጀንነት እያደረጉት ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የትምህርት ስርዓቱ አገሩን የ ሚወድ የአገሩን ህልውና የሚያስከብር ላገሩ አንድነት የሚሰዋ ዜጋ በማፍራት ያለበትን ኃላፊነት አጠናክሮ እንዲወጣም አሳስበዋል።
ለሰራዊቱ ከተደረገው ድጋፍ ውስጥ 29 ሚሊዮን 179ሺ 738 ከ73 ብር በጥሬ ገንዘብ ሲሆን ቀሪው ለሠራዊቱ ስንቅ የሚሆን የአይነት ድጋፎች መሆናቸው ተገልጿል።
የትምህርት ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማቱ ሠራተኞችና አመራሮች ከዚህ ቀደምም ለአገር መከላከያ ሠራዊት በገንዘብና በዓይነት ድጋፍ ማድረጋቸው ይታወቃል።