News Detail

የሀገር ውስጥ ዜና
Apr 12, 2021 327 views

ኢትዮጵያ በዩኔስኮ የስራ አስፈፃሚ ቦርድ ስብሰባን እየተካፈለች ነው፡፡

የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት ዩኔስኮ፣ (UNESCO) 211ኛ የስራ አስፈፃሚ ቦርድ ስብሰባ በበይነመረብ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በዩኔስኮ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት እና የዩኔስኮ የስራ አስፈፃሚ ቦርድ አባል እንዲሁም የትምህርት ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ ( ዶ/ር ኢንጂ ) ዛሬ በተጀመረው  የዩኔስኮ የስራ አስፈፃሚ ቦርድ ስብሰባ ላይ በመካፈል ላይ ይገኛሉ።

የትምህርት ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ በስብሰባው ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ሀገራችን ኢትዮጵያ በትምህርት፣ በሳይንስ፣ በባህልና ቱሪዝም ዘርፎች በማከናወን ላይ ያለችውን ዓበይት ተግባራትን ጠቅሰዋል። 

ከኮቪድ 19 በኋላ የትምህርት ዘርፉን ዳግም ለመክፈትና ለማስቀጠል በመንግስት የተወሰዱ እርምጃዎችን፣ በቱሪዝም ዘርፍ ያለውን የቱሪስቶች ፍሰት  እንዲሁም በትግራይ ክልል ህግን ለማስከበር ከተደረገው ዘመቻ ጋር ተያይዞ በዩኔስኮ የተመዘገቡ ቅርሶች  ደህንነት ዙሪያም ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በጫና ውስጥ ያለውን  የቱሪዝም ዘርፉ ለማነቃቃት መንግስት አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎቸን  በመገንባት እና ክፍት በማድረግ  ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየሰራ መሆኑን እና አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችም በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በሁሉም የዓለም ሀገራት የትምህርት እና የባህልና የቱሪዝም ዘርፉ  ከጤና ባለሙያዎች ቀጥሎ የሁሉም ሀገር መምህራንን ታሳቢ ያደረገ የክትባት አቅርቦት ሊኖር እንደሚገባም ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡

ኮቪድ በጤናው ዘርፍ ላይ ያስከተለውን ጫና በንግግራቸው የጠቀሱት ሚኒስትሩ፣ በተለይም በኮቫክስ (COVAX) የኮቪድ ክትባት አቅርቦት የዓለም አቀፍ የተራድዖ ግብረ-ሀይል በተሰጠ ድጋፍ በኢትዮጵያ ክትባት መሰጠት መጀመሩ መልካም ቢሆንም እስከ ታህሳስ 2014 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ 20% የሀገሪቱን ዜጎች ብቻ ተደራሽ የሚያደርግ ሀብት ብቻ መገኘቱ አዝጋሚ መሆኑን እና በተቃራኒው ያደጉት ሀገራት ከፍተኛ የክትባት ክምችት ላይ መሰማራታቸው ተገቢ አለመሆኑን የዩኔስኮ ቦርድ ድምፁን እንዲያሰማ ሚኒስትሩ ጠይቀዋል።

በ 211ኛው የዩኔስኮ የስራ አስፈፃሚ ቦርድ ስበሰባ ላይ ከሚኒስትሩ በተጨማሪ በፈረንሳይና በዩኔስኮ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሄኖክ ተፈራ የአፍሪካ ሀገራትን በመወከል እየተሳተፉ ይገኛሉ።

 ኢትዮጵያ ከሰሀራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራትን በመወከል የዩኔስኮ የስራ አስፈጻሚ ቦርድ አባል ሆና በማገልገል ላይ ትገኛለች።

Recent News
Follow Us