News Detail
Nov 21, 2025
97 views
የትምህርት ሚኒስትሩ የናይጄሪያ ቴክኒካል ድጋፍ በጎፈቃደኞች ድርጅት ልዑካን ቡድንን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ። የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ከናይጄሪያ ቴክኒክ ድጋፍ በጎፈቃደኞች ድርጅት ልዑክ ጋር በጽ/ቤታቸው ተወያይተዋል።
የሁለቱ አካላት ውይይት ናይጄሪያ ከዚህ ቀደም ለሀገራችን ስትሰጥ የነበረውና ተቋርጦ የቆየውን የበጎ ፈቃደኞች የቴክኒክ ድጋፍ ማስቀጠል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው ።
በዚሁ ጊዜ ናይጄሪያ ከኢትዮጵያጋር የቆየ ወዳጅነት ያላት ሀገር መሆኗን ያነሱት የልዑካን ቡድኑ መሪ ሀገራቸው ከዚህ ቀደም ለኢትዮጵያ የበጎ ፈቃደኞች ቴክኒክ ድጋፍ ስታደርግ መቆየቷን አንስተዋል።
ነገር ግን ይህ የበጎ ፈቃደኞች የቴክኒክ ድጋፍ በተለያየ ምክንያት ተቋርጦ መቆየቱንና አሁን ላይ የናይጄሪያ መንግስት ይህንን በትምህርቱ ዘርፉ የሚያደርገውን የበጎ ፈቃደኞች ቴክኒክ ድጋፍ ማስቀጠል ፍላጎት ያለው በመሆኑ በጎ ፍቃደኞችን ለማሰማራት የሚቻልበትን ሁኔታ ለክቡር ሚኒስትሩ ገልጸውላቸዋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ በበኩላቸው ይህ በትምህርቱ ዘርፍ የሚደረገው የበጎ ፈቃደኞች ቴክኒክ ድጋፍ ሀገራችንን የበለጠ ተጠቃሚ እንድትሆን እንደሚያስችል እምነታቸውን መሆኑ ገልጸዋል።
በተለይም በሀገራችን ለተጀመረው ሪፎርም የሚያስፈልጉትን እንደ ፔትሮ ኬሚካል፣ ማዕድን ልማት፣ ኒውክለር ሳይንስ እና ለመሳሰሉት አዳዲስ የሙያ መስኮች የናይጄሪያ ተሞክሮ አስፈላጊ መሆኑን አንስተውላቸዋል።
በመሆኑም በነዚህ አዳዲስ የትምህርት መስኮች በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው በጎ ፈቃደኛ ሙሁራንን ወደ አገራችን ቢመጡ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ባለሙያዎችን በመላክ ልምድ እንዲወስዱ ቢደርግ ጠቃሚ እንደሚሆንም ለዑካን ቡድኑ ገልጸውላቸዋል።
ለዚህም ተግባራዊነት የልዑካን ቡድኑ መሪና የትምህርት ሚኒስቴር ቴክኒካል ቡድን ከላይ በተጠቀሱት የትምህርት መስኮች በጋራ ለመስራት የሚያስችል ዝርዝር ዝግጅት በቀጣይ እንዲደርግ ሁለቱ አካላት በነበራቸው ውይይት ተስማምተዋል።