News Detail
Nov 29, 2025
31 views
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌስር ብርሃኑ ነጋ ከደቡብ አፍሪካ የመጡ የልዑካን ቡድን አባላትን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል። ሁለቱ አካላት በነበራቸው ውይይትም University of South Africa (UNISA) በኢትዮጵያ እንዴት በትብብር መስራት እንደሚችል ተወያይተዋል።
በዚሁ ጊዜ የልዑካን ቡድኑን የመሩት የUnisa’s Principal and Vice-Chancellor Prof Puleng LenkaBula ፤ UNISA ከዚህ ቀደም ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ባደረገው ስምምነት መሰረት ከ2006 ጀምሮ በትምህርት፣ በምርምር እና በቴክኖሎጂ መስክ በርካታ ተማሪዎችንና የመንግስት ሰራተኞችን ሲያስመርቅ መቆየቱን ለክቡር ሚኒስትሩ አብራርተውላቸዋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው በኢትዮጵያ የነበረው የትምህርት ሥርዓት ከፍተኛ ችግር የነበረበትና በከፍተኛ ትምህርት ዜጎች ዲግሪ በገንዘብ የሚገዙበት ጭምር የነበረ በመሆኑ፤
ይህንን ለማስተካከል በትምህርት ዘርፉ የተለያዩ የትምህርት ጥራትን ሊያረጋግጡ እንዲሁም ብቃት ያላቸው፣ ተወዳዳሪ የሆኑ ዜጎችን ለማፍራት የሚያስችሉ የሪፎርም ሥራዎች እየተተገበሩ መሆኑና በዚህም ለውጦች እየተመዘገቡ መምጣታቸውን ለልዑካን ቡድኑ አብራርተዋል።
በአሁኑ ወቅት ዓለም በፈጣን እድገት ላይ ስትሆን በሌላ በኩል ደግሞ በጣም ውስብስብ እየሆነች መጥታለች ያሉት ሚኒስትሩ UNISA ከ20 ዓመት በፊት በጀመረው ስምምነትና ፕሮግራም መሰረት አሁን ባለው የኢትዮጵያ ፍላጎትና የኢኮኖሚ እድገት ሊቀጥል የማይችል በመሆኑ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጎችን ለማፍራት በሚያስችል መልኩ መታየት እንዳለበት አስገንዝበው በአፍሪካ በትምህርቱ ዘርፍ የሚደረጉ ትብብሮች ይህንን መሰረት ያደረጉ መሆን እንዳለባቸው አሳስበዋል።
አክለውም በትምህርቱ ዘርፍ የሚደረጉ የጋራ ሥራዎችም ሀገራችን ለያዘቻቸው የልማት እቅዶች መሳካት የሚያስፈልግ የሰው ሃይል ልማትን በሚያግዙ የትምህርት መስኮች እንደ ማዕድን፣ ፔትሮ ኬሚካል፣ አግሮ ኢንደስትሪ የመሳሰሉት ላይ ትኩረት ያደረጉ መሆን ይገባቸዋልም ብለዋል።
የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ኮራ ጡሹኔ በበኩላቸው UNISA በሀገራችን ላለፉት 20 ዓመታት ሲሰራ መቆየቱ ቢታወቅም፣ በቀጣይ የኢትዮጵያን የመልማት ፍላጎት መሰረት ባደረገ መልኩ አዲስ ውይይት ማድረግ ይቻላል ብለዋል።
ሁለቱ አካላት በነበራቸው ውይይት የጋራ ኮሚቴ ተቋቁሞ በየትኞቹ ጉዳዮች በትብብር ለመስራት እንደሚቻል እንዲለዩና ለቀጣይ ውይይት መነሻ የሚሆኑ ጉዳዮች እንዲቀርቡ ተስማምተዋል።
በውይይቱ ላይ በኢትዮጵያ የደቡብ አፍሪካ አምባሳደርን ጨምሮ የUNISA ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ አመራሮች ተግኝተዋል።