News Detail
Nov 11, 2025
6 views
የትምህርት ስርዓቱን ከዓለም የአየር ንብረት ፣ የቴክኖሎጂ፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ለውጥ ጋር በሚጣጣም መልኩ መቃኘት እንደሚገባ ተመላከተ። 34ኛው ሀገር አቀፍ የትምህርት ጉባኤ ባለ 12 ነጥብ አቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ እንደገለጹት የትምህርቱን ሥራ ከአየር ንብረት ፣ ቴክኖሎጂና ከዓለም የፖለቲካና የኢኮኖሚ ለውጥ ጋር በሚጣጣም መልኩ መቃኘትና መተግበር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ይህ ጊዜ ለውጦችን በመቋቋም ወደ እድል የሚቀይሩ ፣ አገራቸውን የሚወዱና ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግሩ ዜጎችን ለማፍራት በትጋት የምንሰራበት ወቅት መሆኑንም ፕሮፌሰር ብርሃኑ ተናግረዋል።
በመሆኑም በየደረጃው ያሉ መምምህራን በሚያስተምሩበት ትምህርት አይነት የበቁ ሆነው በመገኘት ሙያቸውን ሊያሳድጉና ሊያስከብሩ እንደሚገባ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።
በተጨማሪም የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለተቋቋሙበት አላማ ቅድሚያ በመስጠት ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም የትምህርት ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የአካል ጉዳተኞችን የመማር ማስተማር ከባቢ ምቹ ለማድረግ አገሪቱ ባላት አቅም ድጋፍ እንደሚደረግም አመልክተዋል።
በበኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፍትሃዊና “ጥራት ያለው ትምህርት ለሁሉም” በሚል መሪቃል የተካሄደው 34ኛው የትምህርት ጉባኤ ባለ 12 ነጥብ አቋም መግለጫ በማውጣትም ተጠናቋል።