News Detail

የሀገር ውስጥ ዜና
Apr 08, 2021 427 views

በሀገር አቀፍ ደረጃ 183 ምስጉን መምህራን ሽልማት እና እውቅና ተሰጣቸው።

ትምህርት ሚነስቴር ከመምህራን ማህበር ጋር በጋራ በመሆን "በቀውስ ውስጥም ሆነን ትውልድን እንቀርፃለን" በሚል መሪ ቃል የመምህራን ቀንን በሀገር አቀፍ ደረጃ አክብሯል።

በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ  እንዲ አይነት እውቅና ሙያውን ወደ ሚገባው ከፍታ ቦታ ያስቀምጠዋል ብለዋል።

ለመምህራን እውቅና  መስጠት ባህል መሆን እንዳለበት የተናገሩት ፕሬዝዳንቷ መምህራኖች የነገ ትውልድ ተረካቢዎችን የሚያፈሩ የሙያ አባቶችና እናቶች በመሆናቸው ሊከበሩ እና ሊመሰገኑ እንደሚገባ ገልፀዋል።

በንግግራቸውም መምህራኖች ትውልድን የመቅረፅ ሃላፊነታቸውን በንቃት  እንዲወጡ  ጥሪ አቅርበዋል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ(ፒ ኤች ዲ)የመምህርነት ሙያ  ክቡር ሙያ፤ የሁሉም ሞያዎች አባት በመሆኑ ለመምህራን ላቅ ያለ ምስጋና እና ክብር ልንሰጣቸው ይገባል ብለዋል።

በ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ  የትምህርት መርሀ ግብር በተስተጓጎለበት ወቅት ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት በመመለስ እና የትምህርት ሂደቱ እንዲቀጥል  በተደረገው ሀገራዊ ጥሪ መምህራን ግዴታቸውን የተወጡ የቁርጥ  ቀን ልጆች ናቸው ሲሉ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። 

መምህራኖችን የማመስገን እና እውቅና የመስጠት መርሀ ግብርም  ቀጣይነት ያለው መሆኑን እንዲሁም የመምህርነት ሙያን ሳቢ ለማድረግ ትምህርት ሚኒስቴር ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም ገልፀዋል።

የኢትዬጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት ዬሀንስ በንቲ(ዶ/ር) በበኩላቸው የመምህራን ቀን አከባበር ዓላማ ለመምህራን እውቅና እና ምስጋና ለማቅረብ እና መምህራን ሀገራዊ ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ ለማቅረብ መሆኑን ተናግረዋል።

የዘንድሮውን የመምህራን ቀንን ትምህርት ሚኒስቴር በሀገር አቀፍ ደረጃ  በባለቤትነት ማክበሩ ቀኑን ልዩ ያደርገዋልም ብለዋል።

በፕሮግራሙም  ከሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ 143 በስራ ላይ ያሉ   ውጤታማ መምህራኖች እና 40 አንጋፋ መምህራኖች የገንዘብ ሽልማት እና እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

በመርሀ ግብሩም  ላይ ለኢትዬጵያ መምህራን ማህበር  መምህራንን ለማመስገን እየሰራ ላለው ስራ የትምሀርት ሚኒስቴር  የ 2ሚሊዬን ብር ድጋፍ አድርጓል።

በዝግጅቱም የኢፌድሪ ፕሬዝዳትን ጨምሮ  የተለያዬ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጠናት፣ መምህራን እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ከዚህ ቀደም በተለያዩ ክልሎች እንዲሁም በከተማ አስተዳደሮች አዘጋጅነት ለመምህራን ምስጋና እና እውቅና  ሲሰጥ መቆየቱ ይታወሳል።

Recent News
Follow Us