News Detail
Mar 07, 2025
100 views
ዩኒቨርሲቲዎች ነፃ ምሁራዊ ውይይት የሚካሄድባቸው የሀገር የሀሳብና የእውቀት መሪ ሊሆኑ እንደሚገባ የትምህርት ሚኒስትሩ አሳሰቡ።
የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች ከደምቢዶሎ ዩኒቨርስቲ አመራሮችና ማህበረሰብ አባላት ጋር ውይይት አካሂደዋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ዩኒቨርሲቲዎች ተልዕኳቸውን በሚገባ እንዲወጡ ከመንደር አስተሳሰብና ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
ዩኒቨርሲቲዎች በነፃነት እውነተኛ ምሁራዊ ውይይት የሚደረግባቸው የዚች ሀገር እውቀት መሪ ሊሆኑ ይገባል፤ ወደዛ እንዲሄዱም እንፈልጋለን ያሉ ሲሆን፤
ዩኒቨርሲቲዎች ትክክልና ስህተትን የሚለዩ ጥሩ ሥነ-ምግባር የተላበሱ ምሩቃንን የሚያፈሩ እንዲሁም ሙስናን የሚቃወሙና የሚከላከሉ ሊሆኑም እንደሚገባም አሳስበዋል።
የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ኮራ ጡሹኔ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲዎች ያላቸውን ሪሶርስ በአግባቡ ለመጠቀም የቅድሚያ ትኩረት ጉዳዮችን ለይተው በመስራት ችግሮችን ደረጃ በደረጃ መፍታት ይጠበቅባቸዋል ፤
በዚህም አዲሱ አመራር የትምህርት ጥራት የሚያረጋግጡ ሥራዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይኖርበታልም ብለዋል።
በከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ የአስተዳደርና መሠረተ ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ ሰለሞን አብርሃ(ዶ/ር) በተቋሙ የታዩ ጠንካራና መሻሻል ያለባቸውን ጉዳዮች ለውይይት መነሻ ያቀረቡ ሲሆን የዩኒቨርስቲው አዲስ አመራሮች ተቋሙን ካለበት ችግር ለማውጣት ጠንክረው መስራት እንዳለባቸው አብራርተዋል።
የዩኒቨርስቲው ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ታደሰ ረጋሳ (ዶ/ር) በበኩላቸው ተቋሙን ለመለወጥ ከሁሉም አመራርና በለድርሻ ጋር በመግባባት ወደ ሥራ መግባታቸውን ገልፀዋል።
የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላትም የተለያዩ ጥያቄዎችን አንስተው በሚመለከታቸው አካላት ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።
የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ አዲስ የአመራር ለውጥ ከተደረገላቸው ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ አንዱ መሆኑ ይታወቃል።