News Detail
Mar 07, 2025
134 views
በአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ የትምህርት መረጃ አስተዳደር ስርዓትን ወጥና ዲጂታላይዝድ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተጠቆመ።
የትምህርት ሚኒስቴር ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የክልልና ከተማ መስተዳድር የትምህርት መረጃ አስተዳደር ባለሙያዎች፣ ስራ ሀላፊዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር እየተሠሩ ባሉ ስራዎች ላይ ምክክር አድርጓል።
በምክክር መድረኩ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ በመገኘት ቁልፍ መልዕክት ያስተላለፉት የትምህርት ሚኒስቴር የስራ አመራር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ይበልጣል አያሌው የትምህርት ዘርፉን የመረጃ አስተዳደር ስርዓት ለማዘመንና ዲጂታላይዝ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች አበረታች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ዋና ስራ አስፈጻሚው በማያያዝም በመከናወን ላይ ያሉ ጅምር ስራዎችን በሚገባው ፍጥነት በማጠናቀቅ የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ የመረጃ አስተዳደር ስርዓቱን ማዘመንና ወደ ስራ ማስገባት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር የአይሲቲና ዲጂታል ትምህርት መሪ ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ዘላለም አሰፋ በበኩላቸው በትምህርት ዘርፉ ያለውን የመረጃ ሥርዓት ለማዘመን እና ዲጂታላይዝ ለማድረግ በርካታ ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን በዚህም መረጃን በሃላፊነት እና በተጠያቂነት በማድረስ ረገድ የሚታዩ ክፍተቶችን ለማረም ጥረት እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
ከትምህርት ቤት ጀምሮ ያለውን የመረጃ ስርዓት በማዘመን፣ ጥራትና ታዓማኒነቱን በማስጠበቅ በወቅቱ ተደራሽ ለማድረግና ጥቅም ላይ ማዋል የሚደረገውን ጥረት ባለድርሻ አካላት እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል።
የትምህርት መረጃ አስተዳደር ስርዓትና የአይሲቲ ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰብስብ ለማ በበኩላቸው በመከናወን ላይ ያሉ ስራዎች የመረጃ ስርዓቱን ወጥና ዲጂታላይዝድ በማድረግ በመረጃ አሰባሰብ አደረጃጀትና ትንተና ተደራሽነትን ለማሳደግ ያስችላል ብለዋል።
በምክክር መድረኩ መረጃ ኦን ላይን (online) ብቻ ሳይሆን ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ኦፍ ላይን (Off line ) እና በሌሎችም አማራጮች በቴክኖሎጂ እንዴት መጠቀምና ሪፖርት ማድረግ እንደሚቻል መመላከቱንም አቶ ሰብስብ ለማ አመላክተዋል።