News Detail
Nov 23, 2024
100 views
የእጅ መታጠብና የንጽህናን አጠባበቅ ልምምዶችን በትምህርት ቤቶች ማስተማር የበሽታዎችን ስርጭትና የተማሪዎችን ከትምህርት ቤት መቅረት እንደሚቀንስ ተገለጸ።
ዓለም አቀፍ የእጅ መታጠብ እና የመጸዳጃ ቤት ቀን በአለርት ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በአገር አቀፍ ደረጃ ተከብሯል፡፡
በኢትዮጵያ የ” WASH” ዩኒሴፍ ኃላፊ ቪክቶር ኪኒያንጆይ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት እጅን በአግባቡ መታጠብና ንጽህናን መጠበቅ በሽታን ከመከላከል ባሻገር ከትምህርት ቤት የመቅረት ምጣኔን ይቀንሳል ብለዋል፡፡ አክለውም በመጀመሪያ ደረጃ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እጅ የመታጠብና የንጽህና አጠባበቅ የእለት ተዕለት ልምምድና ተግባር ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
ዩኒሴፍ የትምህርት ቤቶች የንጽህና አጠባበቅ የስርዓተ ትምህርት አካል መሆን አለበት ብሎ እንደሚያምንም የ” WASH” ዩኒሴፍ ኃላፊ ቪክቶር ኪኒያንጆይ አስረድተዋል፡፡
የጤና ሚኒስቴር ዴኤታው ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በበኩላቸው እጅ በመታጠብ ብቻ በአገራችን ህጻናት፣ ተማሪዎችን እንዲሁም ወጣቶችና አዋቂዎችን በየጊዜው የሚያጠቁ ጉንፋንና መሰል የመተንፈሻ አካላት በሽታዎችን በ1/3ኛ መቀነስ እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡
በወሳኝ ጊዜያት እጅን በውሃና በሳሙና መታጠብ ተቅማጥና ተያያዥ በሽታዎችን እስከ 50 በመቶ እንደሚቀንስ የጠቆሙት ዶ/ር ደረጀ በተገቢው ጊዜ እጅ በመታጠብና የመጸዳጃ ቤት አጠቃቀምን በማሻሻል ጤናማ ለአገር ብልጽግና የራሱን ሃላፊነትና ድርሻ የሚወጣ ማህበረሰብ መፍጠር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የውሃና ኤነርጂ ሚኒስትር ዴኤታው አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዴንጋሞ በበኩላቸው መጸዳጃ ቤቶችን በአግባቡ የመጠቀም ፣ እጅን የመታጠብና ንጽህናን የመጠበቅ ባህልን ማሳደግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ የውሃ አቅርቦት ስፔሺሊስትና ዎሽ አስተባባሪ የሆኑት ወ/ሮ ሉዓም አበበ በበኩላቸው በትምህርት ቤቶች ላይ ንጹህ ውሃ አቅርቦትና ሳኒቴሽን ሀይጂን መሰረተ ልማት በመገንባት ተማሪዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
እጅን በውሃና በሳሙና በመታጠብና የመጸደጃ ቤት አጠቃቀምን በማሻሻል ከንጽህና ጉድለት የሚመጡ በሽታዎችን በመከላከል ተማሪዎችን ከትምህርት ቤት እንዳይቀሩ ማድረግ እንደሚገባም ወ/ሮ ሉዋም ተናግረዋል፡፡
የእጅ መታጠብ ቀን “ንጹህ እጆች ለጤናችን ዋስትና ናቸው” በሚል መሪ ቃል በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ለ16ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደረጃ ደግሞ ለ15ኛ ጊዜ የመጸዳጃ ቤት ቀን ደግሞ “መጸዳጃ ቤትን በንጽህና መያዝና መጠቀም ዘመናዊነት ነው “ በሚል ቃል በዓለም ለ11ኛ ጊዜ ፣ በአገራችን ደግሞ ለ8ኛ ጊዜ በዕለቱ መከበሩ ታውቋል፡፡