News Detail
Nov 18, 2024
79 views
የትምህርት ቤቶች ስፖርት ሊግ ተጀመረ።
ትምህርት ሚኒስቴር ከሁሉም ክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች የትምህርት ቢሮዎች ጋር በመተባበር የትምህርት ቤቶች ስፖርት ሊግን አስጀምሯል።
ተማሪዎች መደበኛ የትምህርት ጊዜያቸውን ሳይጎዱ በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የስፖርት ሊግ መርሃ ግብሩ ተዘጋጅቶ ወደተግባር ገብቷል። የተማሪዎች ከመደበኛ ትምህርትቸው ጎን ለጎን በተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች መሳተፍ የተማሪዎችን አካላዊ፣ ማህበራዊ፣ ስነ ልቦናዊ ጠቀሜታው የጎላ ነው።
ከዚህ አኳያም በ2017 የትምህርት ዘመን በምስራቅ ቀጣና የተደራጀው የሀረሪ ክልል በሁሉም ትምህርት ቤቶች በቮሊቦል፣ በእግር ኳስ፣ በቅርጫት ኳስ፣ በእጅ ኳስ፣ በአትሌትክስ፣ በጂምናስቲክስ፣ በጠረዼዛ ኳስ እና በባህላዊ ስፖርት አይነቶች የክልሉ አመራሮች ፣ የሀይማኖት አባቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና የትምህርት ቤት አመራሮች በተገኙበት በልዩ ልዩ ዝግጅቶች በድምቀትተከፍቷል።
ስፖርታዊ ውድድሩ አመቱን ሙሉ የሚቀጥል ሲሆን ከሀረሪ ክልል በተጨማሪም የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት በተገኙበት የማስጀመሪያ መድረክ ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራ ገብቷል፡፡
በሌሎች የሀገራችን ክፍሎች ደግሞ በደቡብ ቀጣና ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ በደቡብ ኢትዮጵያ በጋሞ ዞንና በደቡብ ኦሞ ዞን የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በቮሊቦልና በእግር ኳስ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል በጉጂ ዞን የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በእግር ኳስ ፣ በቮሊቦል እና በአትሌትክስ ስፖርት በደመቀ ሁኔታ ተጀምሯል፡፡
በሌሎች የቀጣና አደረጃጀቶች ስር የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ስፖርታዊ ውድድሮቹን በቅርቡ የሚያስጀምሩ ይሆናል።