News Detail
Nov 13, 2024
75 views
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እየተተገበሩ ያሉና በቀጣይ ሊተገበሩ በእቅድ የተያዙ የሪፎርም ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሥራ አመራር ቦርድ አባላት ሃላፊነታቸውን እንዲውጡ ተጠየቀ።
ትምህርት ሚኒስቴር ከዩኒቨርሲቲዎች የሥራ አመራር ቦርድ አባላት ጋር በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሪፎርም አተገባበርና ቀጣይ እቅዶች ዙሪያ ምክክር አካሂዷል።
በምክክር መድረኩ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የእውቀትና የምርምር ምንጭ እንዲሆኑ የተለያዩ የሪፎርም አጀንዳዎች ተቀርጸው ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲዎች የአካባቢያቸውን ጸጋ ተጠቅመው የማህበረሰቡን ህይወት የመቀየርና በሁለንተናዊ ሥራዎቻቸው አርዓያ ሆነው ሊሰሩ እንደሚገባ አንስተው ይህንን ሊመጥን የሚችል የለውጥ እርምጃዎች እየተወስዱ እንደሚገኙ አብራርተዋል።
በዚህም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውጤታማ እንዲሆኑ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት በሃላፊነትና በተጠያቂነት ስሜት ዩኒቨርሲቲዎችን ሊመሩ እንደሚገባም ጠይቀዋል።
የዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ አባላት ለሚመሩት ዩኒቨርሲቲ ስኬትም ሆነ ውድቀት ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው አውቀው ሃላፊነትን መውሰድ እንደሚጠበቅባቸውም ተናግረዋል።
የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ኮራ ጡሹኔ በበኩላቸው ”የከፍተኛ ትምህርት ለከፍተኛ ለውጥ’’ በሚል ርዕስ እየተገበሩ ያሉ ሪፎርሞችና ቀጣይ እቅዶችን አቅርበዋል።
በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት በሀገራችን ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች በተሰጣቸው ተልዕኮ መሰረት ሥራቸውን እንዲሰሩ ማድረግና የተጠያቂነት ሥርዓት መዘርጋት እንደሚገባ አንስተው የዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ አባላት በየጊዜው የዩኒቨርሲቲዎችን አፈጻጸም በመገምገም ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው ገልጸዋል።
በዚህም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሥራ አመራር ቦርድ አባላት አደረጃጀት በተቻለ መጠን ከተቋማት የተልዕኮ መስክ አንጻር መደገፍና መከታተል የሚችሉበትን ታሳቢ ያደረገ የሙያ ስብጥር እንዲኖረው ለማድረግም እንደሚሰራ አብራርተዋል።
በሌላ በኩል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያሉበትን ሁኔታ የሚገልጽ የድጋፍና ክትትል ሪፖርት ያቀረቡት በከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ የመሰረተ ልማትና አስተዳደራዊ ጉዳዮች መሪ ሥራ አስፈጻሚ ሰለሞን አብርሃ (ዶ/ር) ቀደም ብለው ወደ ትግበራ የገቡ የሪፎርም ሥራዎች በተጨባጭ ለውጥ እያመጡ መሆናቸውን ጠቅሰው የቅድመ ምረቃ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና ተማሪዎች በትምህርታቸው ላይ እንዲያተኩሩ ማድረጉን ለአብነት አንስተዋል።
በምክክር መድረኩ የተሳተፉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሥራ አመራር ቦርድ አባላት የተለያዩ ጥያቂዎችና አስተያየቶችን አንስተው ውይይት ተድርጎባቸዋል።
በውይይቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሥራ አመራር ቦርድ አባላትና የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች ተሳታፊ ሆነዋል።