News Detail

National News
Nov 13, 2024 68 views

9ኛው ሀገር አቀፍ የተማሪዎችና መምህራን የፈጠራ ሥራዎች ውድድርና አውደርዕይ ተጀመረ

9ኛው ሀገር አቀፍ የተማሪዎችና መምህራን የፈጠራ ሥራዎች ውድድርና አውደርዕይ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ አስተናጋጅነት ተጀምሯል፡፡
በትምህርት ሚኒስቴር የመምህራንና ትምህርት አመራር ልማት መሪ አስፈፃሚ ዶ/ር ሙሉቀን ንጋቱ የፈጠራ ሥራዎች ውድድርና አውደርዕዩን በከፈቱበት ወቅት ውድድሩና አውደርዕዩ ተማሪዎችንና መምህራንን በማበረታታትና በማነቃቃት ለተሻለ የፈጠራ ሥራዎች ዝግጁ እንዲሆኑ ለማስቻል የሚረዳ በመሆኑ ትምህርት ሚኒስቴርም የሚያደርገውን ድጋፍና ክትትል አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል።
ዶ/ር ሙሉቀን አያይዘውም መምህራንና ተማሪዎች መድረኩን ይበልጥ ለእርስ በርስ የልምድ ልውውጥ ሊጠቀሙበት እንደሚገባ ጠቅሰው የፈጠራ ሥራዎችም ወቅታዊ ችግሮችን በመፍታት ሂደት የነገይቱን ሀገራችን ችግሮች ታሳቢ ባደረገ መልኩ አቅም እየገነቡ በመሄድ ላይ ያተኮረ ሊሆን እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
አገር አቀፍ የስቲም ፓወር ዳይሬከተር ዶ/ር ስሜነው ቀስቅስ በበኩላቸው የሳይንስ ትምህርቶችን በተግባር አስደግፎ በማስተማርና ከትምህርት ቤት እስከ ዩኒቨርሲቲዎች ያሉ የፈጠራ ሥራዎችን የመደገፍ ሥራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ጠቅሰው እስከ አሁን የተሠሩ ሥራዎች ተስፋ ሰጪ እንደሆኑ በማሳያነት ሊቀርቡ የሚችሉ በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ ተማሪዎችን ማፍራት የተቻለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር ስሜነው አክለውም በአሁኑ ወቅት በልጽገው የምናያቸው አገሮች እዚህ ደረጃ ሊደርሱ ያቻሉበት ዋነኛው ምክንያት ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው በመሥራታቸው እንደሆነ ጠቁመው የአገራችንን የፈጠራ ሥራዎች ይበልጥ ለማበረታታትና ውጤታማነቱንም ለመጨመር ከትምህርት ቤት እስከ አገር አቀፍ ደርጃ ያሉትን መሰል መድረኮች ከማጥናከር ጎን ለጎን በአህጉርና አለም አቀፍ ደረጃም ጭምር ለማመቻቸት ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል።
የሥራ ፈጠራ ውድድሩና አውደርዕዩ ለቀጣይ ሦስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ መሆኑም ተመላክቷል።
Recent News
Follow Us