News Detail
May 17, 2024
1.2K views
ዩኒቨርሲቲዎች ከተሰጣቸው ተልዕኮና ቁልፍ የለውጥ አጀንዳዎች አንፃር በውጤት እየተለኩ የሚሄዱበት የአሰራር ሥርዓት እንደሚዘረጋ ተገለፀ።
በመቐለ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ባለው የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች ፎረም ዩኒቨርሲቲዎች ከተሰጣቸው ተልዕኮና ቁልፍ የለውጥ አጀንዳዎች አንፃር በውጤት እየተለኩ የሚሄዱበት የአሰራር ሥርዓት እንደሚዘረጋ ተገለጿል።
የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ኮራ ጡሽኔ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በርካታ ሥራዎችን የሰሩ ቢሆንም ተቋማቱ የሀገሪቱን ችግሮች የሚፈቱ፣ ሥራ ፈጣሪና በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ የሆኑ የሰው ሀይል ማፍራት እንዲችሉ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲዎቹ በለውጡ ጎዳና በፍጥነት ሄደው በዓለም ተወዳዳሪ ተቋማት እንዲሆኑና ተልኳቸውን በሚገባ እንዲወጡ ቁልፍ የለውጥ አጀንዳዎች ተቀርፀው ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን ገልፀዋል።
የዩኒቨርስቲዎች እድገት፣ ስኬት እና ውጤት መለካት መቻል አለበት ያሉት ሚኒስትር ደኤታው ለዚህ የሚረዱ ቁልፍ የውጤት መለኪያ አመላካች መስፈርቶች መዘጋጀታቸውን አንስተዋል።
በዚህም የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶቹ በተዘጋጁት ቁልፍ የውጤት መለኪያ አመላካች መስፈርቶች ላይ ውይይት በማድረግ ከሥምምነት ከተደረሰ በኋላ ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ ፕሬዚዳንቶቹ ውል የሚገቡ ይሆናልም ብለዋል።
በቀጣይ በትምህርት ሚኒስቴርና በዩኒቨርሲቲዎቹ የሚፈረመው የውል ስምምነት ኃላፊነትን በአግባቡ ለመወጣት፣ ሪፎርሞቹን ወደ መሬት ለማውረድና በሂደት የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የሚያስችልም ነው ተብሏል