News Detail
Nov 05, 2025
31 views
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሥርዓተ ትምህርት ውጤት ተኮር እንዲሆን ክለሳ እየተደረገበት መሆኑ ተገለጸ፤ የሚከለሰው ስርዓተ ትምህርትም በ2018 የትምህርት ዘመን ዩኒቨርስቲ የገቡ ተማሪዎች የአንደኛ ዓመት ትምህርታቸውን ሲጨርሱ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል።
የአካዳሚክ ጉዳዮች መሪ ስራ አስፈጻሚ ኤባ ሚጀና (ዶ/ር) የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ተልዕኮ መሰረት ባደረገ መልኩ ስርዓተ ትምህርቱን የመከለስ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የዩኒቨርስቲዎቹን ስርዓተ ትምህርት ውጤት ተኮር አድርጎ መከለስ ያስፈለገው የቀድሞዎቹ ስርዓተ ትምህርቶች ዘመኑን ያልዋጁና ከ21ኛው ክፍለ ዘመን ጋር በአግባቡ ያልተቃኙ በመሆናቸው ነው።
አዲሱ የውጤት ተኮር ስርዓተ ትምህርት ተመራቂዎች በትምህርት ፕሮግራሞቹ መጨረሻ ሊኖራቸው የሚገባውን እውቀት፣ ክህሎትና አመለካከት በአግባቡ የፈተሸ መሆኑን መሪ ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡
የስርዓተ ትምህርት ፕሮግራሞች ዴስክ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ነገዎ በበኩላቸው ውጤት ተኮር የሆነው ስርዓተ ትምህርት ሙያና ተግባር ተኮር መሆኑን ጠቅሰው ስራ ፈላጊ ብቻ ሳይሆን ስራ ፈጣሪ ምሩቃንን ማፍራት እንደሚያስችል ተናግረዋል።
በሁለት ዙሮች እስካሁን 55 የትምህርት ፕሮግራሞች መከለሳቸውን አንስተው እስከ ዓመቱ መጨረሻም ከ80 የሚበልጡ ፕሮግራሞች እንደሚከለሱ አብራርተዋል፡፡
አዲስ የተከለሱት የትምህርት ፕሮግራሞች በ2018 የትምህርት ዘመን ዩኒቨርስቲ የገቡ የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች የአንደኛ ዓመት ትምህርታቸውን ሲጨርሱ ተግባራዊ እንደሚደረጉም ተጠቅሷል።
የስርዓተ ትምህርት ፕሮግራሞች ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ በሱፈቃድ ሃይለማርያም ለስርዓተ ትምህርት ክለሳው ለቅድመ ምረቃ ፕሮግራሞች መሰረታዊ የሆኑ የተማሪዎች ብቃት መለኪያ (competency) ዝግጅት መከናወኑን ጠቁመዋል።