News Detail
Nov 04, 2025
25 views
በመምህራን የትምህርት ዝግጅትና ልማት ላይ ያተኮረ አለም አቀፍ ጉባኤ በአዲስ አበባ ተካሄደ።
“Educators shaping futures" በሚል መሪ ቃል በመምህራን የትምህርት ዝግጅትና ልማት ላይ ያተኮረ አለም አቀፍ የትምህርት ጉባኤ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
ትምህርት ሚኒስቴር ከአለም ባንክና ከሌሎች ተባባሪ አካላት ጋር በጋራ ባዘጋጀው በዚህ አለም አቀፍ ጉባኤ ላይ የበርካታ ሀገራት የትምህርት ባለሙያዎችና ስራ ሀላፊዎች ተሳትፈዋል።
በጉባኤው መክፈቻ ላይ በመገኘት መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ኮራ ጡሹኔ ለትምህርት ጥራት መሳካት መምህራን ቁልፍ ሚና ያላቸው በመሆኑ መምህራንን ማብቃትና መደገፍ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚና መሆኑን አመላክተው በዚህም የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
መንግስት ለትምህርቱ ዘርፍ በሰጠው ትኩረት በርካታ የሪፎርም ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንና ከነዚህም አንዱ የመምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮችን አቅም መገንባት መሆኑን አንስተው መምህራኑ እውቀትን ከማስተላለፍ ባለፈ ትውልዱ የጽናትና ተስፋ ተምሳሌት ሆኖ እንዲቀረጽ የሚረዱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በመከናወን ላይ ያሉት የሪፎርም ስራዎችም የትምህርት ጥራትና አግባብነትን ከሀገራዊ የልማት ፕሮግራሞች ጋር በማዋደድ እውቀት መር ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚደረጉ ጥረቶችን የሚደግፍ መሆናቸውን ሚኒስትር ዴኤታው አያይዘው ገልጸዋል።
መሠል አለም አቀፍ ምክክሮች ልምድና አሠራሮችን ለማወቅና ለመለዋወጥ በር የሚከፍቱ በመሆኑ ለዝግጅቱ መሳካት ጥረት ያደረጉ ወገኖችንም አመስግነዋል።
የአለም ባንክ ዲቪዥን ዳይሬክተር ሜሪያም ሳሊም በበኩላቸው "Universal Education" ን በ2030 ለማሳካት ዓለማችን ተጨማሪ 44 ሚሊየን መምህራን የሚያስፈልጋት መሆኑን የገለጹ ሲሆን ለዚህም አዳዲስ መምህራን ወደ ዘርፉ የሚቀላቀሉበትን አማራጮች ማብዛት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የወደፊቱ ትውልድ የሚወሠነው አሁን ላይ ባለን የመምህራን ዝግጅት፣ ብቃትና ልማት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ መምህራንን ማብቃትና መደገፍ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
በጉባኤው 271 ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የተውጣጡእና ከ150 በላይ የሚሆኑ በሀገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የዘርፉ ተዋንያኖች የተሳተፉበት መሆኑም ተመላክቷል።