News Detail
Oct 31, 2025
21 views
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለተመራቂዎች የመዳረሻ ጥናት (Tracer Study) ትኩረት እንዲሰጡ ትምህርት ሚኒስቴር አሳሰበ፤ የ2016 ምሩቃን የመዳረሻ ጥናት (Tracer Study) ከተያዘው ጥቅምት እስከ መጪው ሚያዚያ ወር እንደሚካሄድ ተጠቁሟል።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለተመራቂዎች የመዳረሻ ጥናት (Tracer Study) ማድረግ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሂዷል።
በመደረኩ የተገኙት የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ኮራ ጡሹኔ የከፍተኛ ትምህርት ተማራቂዎች የመዳረሻ ጥናት የትምህርት ጥራት ማስጠበቂያ አንዱ መንገድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ፕሮግራሞቻቸውን የመዳረሻ ጥናት ካላካሄዱ ምን እየሰሩ እንደሆነ ለማወቅ እንደሚቸገሩና በገበያው የማይፈለግ የሰው ሀብት ሊያሰለጥኑ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም ሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለተመራቂዎች የመዳረሻ ጥናት (Tracer Study) ትኩረት በመስጠት በትምህርት ፕሮግራም ደረጃ ወጥ በሆነ መንገድ ሊሰሩ እንደሚገባ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አሳስበዋል፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረ ህይወት በበኩላቸው የመዳረሻ ጥናት (Tracer Study) ለፖሊሲ ውሳኔ ፣ ለስርዓተ ትምህርት ክለሳና ለሌሎችም አገራዊ እቅዶች ግብዓት ስለሚሆን በተቀናጀ አግባብ ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በሌላ በኩል የአካዳሚክ ጉዳዮች መሪ ስራ አስፈጻሚ ኤባ ሚጀና (ዶ/ር) የመዳረሻ ጥናት (Tracer Study) የአካዳሚክ ዋና ስራ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች በዚህ ጉዳይ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
አያይዘውም የ2016 ተመራቂዎች የመዳረሻ ጥናት በሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከጥቅምት እስከ ሚያዚያ 2018 ዓ.ም ድረስ ወጥ በሆነ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት መካሄድ እንዳለበትም ዶክተር ኤባ ተናግረዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የሁሉም ዩኒቨርስቲዎች የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንቶች እና አካዳሚክ ፕሮግራም ዳይሬክተሮች የተገኙ ሲሆን መዳረሻ ጥናትን በሚመለከት ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡