News Detail
Oct 08, 2025
34 views
ልጆቻችንን በጥራት ካስተማርናቸው በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የመወዳደር ብቃትና ችሎታ አላቸው፤ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የሆጤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የማስፋፊያ ግንባታ ተጠናቆ ተመርቋል።
በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት ደርሶበት የነበረው የሆጤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የማስፋፊያ ግንባታ የትምህርት ሚኒስቴርና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ተመርቋል።
በዚሁ ጊዜ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በአማራ ክልል በሰሜኑ ጦርነት የተጎዱ 45 ትምህርት ቤቶች ግንባታ መጠናቃቸውንና ሰባት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ደግሞ እየተገነቡ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
ወደፊት ይችን ሀገር የሚመሩ ልጆችን ለማፍራት በትኩረት እየተሠራ ነው ያሉት ሚኒስትሩ የአንድ ሀገር እድገት የሚረጋገጠው በትምህርት ላይ በሚሰራ ስራ በመሆኑ የትምህርት ስብራቱን ለማስተካል የተለያዩ የለውጥ እርምጃዎች እየተተገበሩ መሆኑን አንስተዋል።
በዚህም ትልቅ ለውጥ እየታየ መምጣቱን ጠቅሰው ልጆቻችንን በጥራት ከአስተማርናቸው ከየትኛውም ዓለም ያላነሰ ተፈጥሯዊ ችሎታ አላቸው፤ ለዚህም ሁላችንም ሃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል።
ተማሪዎች በላባችሁና በጥረታችሁ ሰርታችሁ ያገኛችሁት እውቀት ከናንተ ጋር የሚቆይ በመሆኑ ጠንክራችሁ ተማሩ ያሉ ሲሆን የትምህርት ሥርዓቱን ለማሻሻል የመምህራን ኃላፊነት ትልቅ በመሆኑ መምህራን ለልጆቹ የወደፊት ህይወት መቃናት የድርሻቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድ ማዕረግ ማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው በሰሜኑ ጦርነት የወደሙ ትምህርት ቤቶችን ለመጠገን የትምህርት ሚኒስቴር ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
መሠል ተግባራት በመንግስት አቅም ብቻ የሚከናወን አይደለም ያሉት ቢሮ ኃላፊዋ ለዚህም የክልሉ ተወላጆች፣ ባለሀብቶች ፣ የዲያስፖራ አባላት እንዲሁም ማህበረሰቡ ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
ከትምህርት ቤት ግንባታ በተጨማሪ የክልሉ ልጆች እንደ ሌላው ተወዳድረው ማደግ ይፈልጋሉ፤ በመሆኑም ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ ለዚህ ሁሉም እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል።
የደሴ ከተማ ተቀዳሚ ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ በበኩላቸው ትምህርት ሚኒስቴር ላደረገው ድጋፍ አመስግነው ከተማ አስተዳዱሩ ለትምህርቱ ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።