News Detail
Oct 06, 2025
38 views
በሳለፍነው ዓመት መንግስት ለትምህርት ዘርፉ ልዩ ትኩረት ስጥቶ መስራቱን የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀስላሴ ገልጹ።
የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀስላሴ የህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የ2018 ዓ.ም የሥራ ዘመን መክፈቻ ላይ ባዳርጉት ንግግር ባለፈው ዓመት መንግስት ለትምህርት ዘርፉ ልዩ ትኩረት ስጥቶ መስራቱ ተናግረዋል።
በትውልዶች ውስጥ የሚስተዋለው የእሴት መሸርሸር ዋናውና መነሻው የትምህርት ጥራት ችግር እንደሆነ መንግስት እንደሚያመን አንስተው ይህንን ሳንካ ለመቅረፍ ባለፈው ዓመት በትምህርት ጥራት ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራቱን ገልጸዋል።
በተለይም መንግስት አዲስ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ቀርጾ ተግባራዊ ማድረጉን፣ የ”ትምህርት ለትውልድ” በሚል መሪ ቃል ማህበረሰቡን በማንቀሳቀስ የትምህርት ተደራሽነትን የማረጋገጥ ስራ መስራቱን አብራርተዋል።
አያይዘውም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ተማሪዎችም በትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም ከትምህርት ቤት እንዳይቀሩ ማድረጉን ጠቅሰው ይህ ፕሮግራምም አለም አቀፍ እውቅና ማግኘቱንም አንስተዋል።
ክቡር ፕሪዚዳንቱ በ2018 በጀት ዓመትም መንግስት ለትምህርት ዘርፉ የሚሰጠውን ትኩረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመው ማህበራዊ ትስስራችንን በማጠናከር፣ ነባርና አዳዲስ ማህበረሰባዊ ጸጋዎቻችንን በመትከል፣ የነበሩትን ከፍ አድርጎ በማቆየት ለቀጣዩ ትውልድ እንዲሸጋጋሩ መንግስት አበክሮ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በዚህም የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ መንግስት ደረጃቸውን የጠበቁ ቅድመ መደበኛና መደበኛ ትምህርት ቤቶች ግንባታን እንደሚያስፋፋ፣
የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ተቋማት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ የሚያስፈልጉ ክህሎት ያላቸውና ውጤታማ ባለሙያዎችን በሚያፈሩ መልኩ እንደሚቃኙ፣
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአካዳሚክ ነጻነታቸው ተጠብቆ እንዲሰሩ የአስተዳደርና የሰው ሃይል ልማታቸው የተሻሻለ እንዲሆን በትኩረት እንደሚሰራም አንስተዋል።
በመጨረሻም በአርብቶ አደር አካባቢዎች የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፈፋት በልዩ ሁኔታ የተቀረጸ እቅድ መኖሩን ጠቅሰው የቅድመ አንደኛ፣ የአንደኛ ደረጃና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት እንዲሁም የሴቶች ትምህርት ተሳትፎ እንዲሻሻል ይደረጋል ብለዋል።