News Detail
Jun 25, 2025
26 views
ኦስትሪያ እና ኢትዮጵያ በከፍተኛ ትምህርቱ ዘርፍ በትብብር ለመሥራት የሚያስችላቸውን ውይይት አካሄዱ።
የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ኮራ ጡሹኔ በኦስትሪያ ምክትል የፋይናንስ ሚኒስትር ‘H.E. Andreas REICHHARDT’ የተመራ ከፍተኛ የልዑካን ቡድንን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
በዚሁ ወቅት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ የትምህርት ጥራትና ብቃትን ለማረጋገጥ እየተተገበሩ ያሉ ሪፎርሞችን ለልዑካን ቡድኑ አብራርተውላቸዋል።
በተለይም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን በተልዕኮና ትኩረት መስክ በመለየት በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን አንስተው በዘርፉ የበለጠ ውጤታማ ለመሆን በትብብር የሚሰሩ ተግባራት መኖራቸውንም አብራርተዋል።
የኦስትሪያ ምክትል የፋይናን ሚኒስትር H.E. Andreas REICHHARDT በበኩላቸው ኦስትሪያና ኢትዮጵያ በትምህርት ዘርፍ የቆየ ትብብር እንደነበራቸው አንስተው ይህንን ትብብር የበለጠ አጠናክረው መቀጠል እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የኦስትሪያ አምባሳደር ሲሞን ክናፕ ደግሞ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ሲሰሩ መቆየታቸውን ጠቅሰው የዩኒቨርሲቲ ዩኒቨርስቲ ትብብርን በማጠናከር በከፍተኛ ትምህርት ልማትና በጥናትና ምርምር ዘርፍ በትብብር መስራት እንደሚፈልጉም አንስተዋል።
ሁለቱ አካላት በነበራቸው ውይይት በከፍተኛ ትምህርት አስተዳደር፣ በአይሲቲ ልማት እንዲሁም በምርምርና ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት በጋራ መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይም ውይይት ማድረጋቸው ተገልጿል።