News Detail

National News
Dec 24, 2024 60 views

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ስራ በውጤታማነት ለመፈጸም የሚያስችል የአሰራር ስርዓት ለመዘርጋት እየተሰራ ነው።

በትምህርት ሚኒስቴርና በሁሉም የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከል ነገ ታህሳስ 16/2017 ዓ.ም የሚፈረመው ስምምነት ተቋማት ብቃትና ችሎታ ያላቸው ምሩቃንን በማፍራት ሂደት ውስጥ ተጠያቂነትን ከማስፈን ባለፈ ውጤታማነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል እንደሆነ ተጠቁሟል።
የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒሰትር ዴኤታ ክቡር አቶ ኮራ ጡሹኔ በቁልፍ የአፈጻጸም አመላካቾች / Key Performance Indicators / 47 ዩኒቨርስቲዎች ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር ድርድር ባደረጉበት ወቅት እንደገለጹት ከተያዘው 2017 ዓ.ም ጀምሮ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሳይንሳዊና ዓለም አቀፋዊ መለኪያች ላይ ያተኮረ እድገት እንዲኖራቸው እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ዩኒቨርስቲዎች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪና ለስራ ገበያው የሚመጥን ብቃትና ችሎታ ያላቸው ምሩቃንን ማፍራት እንዲችሉ ከተያዘው 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ስራን በውጤት መምራት ወደሚያስችል ስርዓት ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ተቋማቱ ስራን በውጤት መምራት ወደሚያችል ስርዓት ማስገባት በሙያዊና ክህሎታዊ ስራዎች እንዲሁም በልህቀት ላይ በማተኮር የአገሪቱን ችግሮች መፍታት የሚችሉ ችግር ፈቺ ምርምሮችን በማድረግ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚን የማልማት ስራ ላይ የበኩላቸውን ወሳኝ ሚና እንዲጫወቱ እንደሚያስችላቸው ክቡር አቶ ኮራ ገልጸዋል፡፡
ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግልጽነትና ተጠያቂነትን ያሰፈነ አመራር እንዲከተሉ ፣ አገሪቱ ለምታወጣው ሀብት ተመጣጣኝ ውጤት እንዲያስገኙ የአፈጻጸም አቅማቸው እንዲገመገምና ለስኬቱም እውቅና እና ሽልማት እንዲያገኙ እንደሚያግዝም ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አመልክተዋል፡፡
የጅጅጋ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር በሽር አብዱላሂ በዚሁ ጊዜ ሲናገሩ ስምምነቱ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ስራዎችን ከስር ከመሰረታቸው በአግባቡ በመያዝ ከሚፈለገው ግብ ላይ ለመድረስና የተጠያቂነትና ውጤታማ የሀብት አጠቃቀም ስርዓት እንዲኖር እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡
የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ብርሃነ መስቀል ጠና በበኩላቸው ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርስቲ በትምህርት ባለሙያዎችና በመምህራን ትምህርት ላይ አተኩሮ የሚሰራ ተቋም እንደመሆኑ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር ድርድርና ስምምነት የተደረገባቸው ቁልፍ የአፈጻጸም አመላካቾች ስራን ቆጥሮ በመረከብ በውጤታማነት ለመፈጸም እንደሚያችል ተናግረዋል፡፡
የቦንጋ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጴጥሮስ ወ/ ጊዮርጊስ ቁልፍ የአፈጻጸም መለኪያዎች ዩኒቨርስቲዎች ወዴት እንደሚሄዱና የት ቦታ ለመድረስ ማቀድ እንዳለባቸው የሚያስገድድ ውል መሆኑን ጠቁመው ከትምህርት ተቋማት ውጪ የሚገኙ ሌሎች ተቋማትም ቢተገብሩት ውጤታማ እንደሚያደርጋቸው አስረድተዋል፡፡
ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ስራን በውጤት መምራት ወደሚያችል ስርዓት ለማስገባት ሚያስችለው / KPI / ስምምነት 47ቱም የመንግስት ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንቶችና የቦርድ ሰብሳቢዎች ከትምህርት ሚኒስትሩ ክቡር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ጋር በነገው እለት በሚኖር ስነ ስርዓት በይፋ ይፈራረማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
Recent News
Follow Us