News Detail

National News
Oct 13, 2022 2.5K views

በከፍተኛ ትምህርትና ምርምር ተቋማት እና በሙያ ማህበራት ለሚዘጋጁ የምርምር ጆርናሎች ግምገማና እውቅና ስርዓት በማበጀት የምርምር ጆርናሎችን ተቀባይነት፣ ጥራት እና እይታን ማሳደግ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

ትምህርት ሚኒስቴር በብሄራዊ ምርምር ጆርናሎች ግምገማና እውቅና አሰጣጥ ስርዓት ፣ ወቅታዊ ሁኔታና ተስፋዎቻቸው ዙሪያ አውደ ጥናት አካሂዷል፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ በምርምር ተቋማት እና በሙያ ማህበራት የሚሰሩ ምርምሮችንና የጥናት ህትመቶችን ለዓለም ተደራሽ በማድረግ ቅቡልነታቸውን ማሳደግ ይገባል ብለዋል፡፡
በአገሪቱ የከፍተኛ የትምህርትና ምርምር ተቋማት እና በሙያ ማህበራት በምርምር ስራ የሚሳተፉ በርካታ ምሁራንና ተመራማሪዎች ቢኖሩም በአለም አቀፍ ምርምር ጆርናሎች ላይ የሚደረገው አስተዋጽኦ ግን አነስተኛ መሆኑን ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ጠቁመዋል፡፡
የአገር ውስጥ የምርምር ጆርናሎች ጥራትና ደረጃቸውን ጠብቀው በአገሪቱ በሚቋቋም የምርምር ጆርናሎች ድረ-ገጽ እና መረጃ ቋት ውስጥ እንዲመዘገቡና ተደራሽ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል ፡፡
አገር ውስጥ የሚታተሙ የምርምር ስራዎች በዓለም አቀፍ የምርምር ጆርናሎች መረጃ ቋት ውስጥ በስፋት እንዲካተቱ የሚያበረታታ የአሰራር ስርዓት ማበጀት እንደሚያስፈልግም በመድረኩ ተነስቷል ፡፡
በመሆኑም የጆርናሎችን ጥራትና እይታ በሚያሳድግ ውድድርንና ትብብርን በሚያረጋግጥ መልኩ የምርምር ስራዎች ሊሰሩ እና እውቅና ሊሰጣቸው እንደሚገባም ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል፡፡
የምርምርና ማህበረሰብ ጉድኝት ጉዳዮች መሪ ስራ አስፈጻሚ ሰለሞን ቢኖር (ዶ/ር) በበኩላቸው የዚህ የጆርናሎች ግምገማና እውቅና አሰጣጥ ስርዓት አውደ ጥናት ዋና ኣላማ የጆርናሎችን ጥራት እና እይታን በመጨመር በዓለም አቀፍ ምርምር መረጃ ስርዓት (International Indexing Databases) ለመካተት በትጋት እንዲሰሩ ማድረግ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ ምርምር ጆርናሎችን ምዘናና ፍተሻ እንዲሁም እውቅና አሰጣጥ ስርዓት በመዘርጋት ከደቡብ አፍሪካ ቀጥሎ ሁለተኛዋ አገር መሆኗን አስረድተዋል፡፡
በአገር ውስጥ ከሚታተሙ 200 በላይ ምርምር ጆርናሎች መካከል ተገቢውን መስፈርት ያሟሉ 39 የምርምር ጆርናሎች እውቅና ማግኘታቸውንም ዶ/ር ሰለሞን ተናግረዋል፡፡
በአውደ ጥናቱ ላይ ተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ከምርምር ማዕከላትና ከሙያ ማህበራት የተወከሉ ተመራማሪዎችና የምርምር ጆርናል ዋና አርታኢዎች ተሳታፊዎች ሆነዋል፡፡
Recent News
Follow Us