News Detail
Oct 13, 2022
2.5K views
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፋንታ ማንደፍሮ(ዶ/ር) የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስፈተን ያደረገውን የቅድመ ዝግጅት ጎበኙ
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፋንታ ማንደፍሮ (ዶ/ር) ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስፈተን ያደረገውን የቅድመ ዝግጅት ስራ ትናንት ማምሻውን ተመልክተዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተናን በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንዲፈተኑ መደረጉ ዓላማዎች ተማሪዎች ፈተናን በራሳቸው ሰርተው ማለፍ የሚችሉበትን ባህል መመለስ እና ፈተናን ከማጭበርበርና ከስርቆት ነጻ የማድረግ መሆኑን ገልጸዋል ።
ከዚህ በተጨማሪ ፈተናን በመስረቅ ወይም የተሳሳቱ መልሶችን በማህበራዊ ትስስር ገጾች በማሰራጨት ተማሪዎች በራሳቸው ተማምነው እንዳይሰሩ የሚደረግበትንና የሚደርስባቸውን የስነ ልቦና ጫና ለማስቀረት እንደሚያስችል ዶ/ር ፋንታ አስረድተዋል።
የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ተማሪዎች ተቀብሎ እንደሚያስፈትን ጠቅሰው፤ ለዚህም የቅድመ ዝግጅት ሥራውን በአካል ተገኝተው መመልከታቸውን ጠቅሰዋል።
በተለይ የተማሪዎችን የመፈተኛ፣ የመኝታና የመመገቢያ ክፍሎች መጎብኘታቸውን ገልጸው ጥሩ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
ብሔራዊ ፈተናው ያለምንም እንከን በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን በየደረጃው ያለው አመራር ሚናውን ሊወጣ እንደሚገባ አመልክተዋል።
የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያው ዙር ከ35 ሺህ በላይ ተማሪዎችን እንደሚያስፈትን የገለጹት የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር እሰይ ከበደ ናቸው።
ዩኒቨርሲቲው በሁለት ዙር ከ60 ሺህ በላይ ተማሪዎችን የሚያስፈትን ሲሆን በአሁኑ ወቅት ለተማሪዎች የመኝታ፣ የመመገቢያ፣ የመፈተኛና ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶች የሚሰጡ ክፍሎች ዝግጅት ተጠናቋል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶ/ር ማተብ ታፈረ በበኩላቸው የቅድመ ዝግጅት ሥራው ተማሪዎች ለፈተና ከሚመጡበት ትምህርት ቤት ጀምሮ መደረጉንና በጥሩ ሁኔታ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
በአንዳንድ አካባቢዎች የትራንስፖርት ችግር በተወሰነ ደረጃ ሊገጥም እንደሚችል ጠቁመው፣ "ችግሩን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ርብርብ እየተደረገ ነው" ብለዋል።
በአማራ ክልል 290 ሺህ የሚደርሱ ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ይፈተናሉ።
ምንጭ;- የባህርዳር ዩኒቨርስቲ ህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት