News Detail

National News
Mar 31, 2021 692 views

ሀገር አቀፍ የትምህርት ብርሃን ምዘና መርሀ ግብር በይፋ ተጀመረ

ትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ብርሀን ምዘና የማስጀመሪያ መርሀ ግብርን በይፋ አስጀምሯል ።
በመረሀ ግብሩ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር እና የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ደመቀ መኮንን፣ የህዝብ ተወካዬች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት እና ሌሎች ከፍተኛ የፌደራል፣ የከተማ አስተዳደሮች እና የክልል አመራሮች ፣ የሀይማኖት አባቶች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
 
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር እና የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ደመቀ መኮንን የምዘናው ስርዓቱ መደበኛ ባልሆኑ መንገዶች እውቀትን ያገኙ ዜጎችን በማነቃቃት ሌሎች ዜጎችም ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ እና መደበኛ እውቀት እንዲያገኙ እንደሚያስችል ገልፀዋል።
 
የትምህርት ብርሀን ምዘና የሀገራችንን የመማር ምጣኔ የሚያሳድግ በመሆኑ ሰው ተኮር የሆነ ስራ ዎችን በመስራት የተማረ የሰው ሃይልን የማፍራት ተልኳችንን መወጣት አለብን ብለዋል።
 
የትምህርት ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ፒ ኤች ዲ) የትምህርት ብርሀን ምዘና የትምህርት ዘርፉ አንዱ የለውጥ አካል መሆኑን ገልፀው በተለያዩ የሙያ ዘርፍ ላይ ያሉ ማንበብ ፣ መፃፍ እና ማስላት የሚችሉ ነገር ግን ያልተመዘኑ እና እውቅና ያላገኙ ዜጎች ተመዝነው እውቅና እንዲያገኙ የሚያደርግ መሆኑን ገልፀዋል።
 
መደበኛ ባልሆኑ መንገዶች ትምህርትን በመስጠት የሀይማኖት ተቋማቶች ከፍተኛ ስራዎችን ሲሰሩ መቆየታቸውን እና በዚህም ማንበብ ፣ መፃፍ እና ማስላት የሚችሉ ዜጎች መፈጠራቸውን ሚነስትሩ ተናግረዋል።
 
ንቅናቄው ቀጣይነት ያለው እና ሁሉም ማንበብ እና መፃፍ የሚችል ዜጋ በዚህ የምዘና ስርዓት በማለፍ በተሰማሩበት የሙያ መስክ ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል።
 
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን ህዝቡ ይህንን እድል እንዲጠቀምበት ጥሪ በማስተላለፍ መርሀ ግብሩን በይፋ አስጀምረዋል።
የትምህርትብርሀን ምዘና ማንበብ ፣መፃፍ እና ማስላት የሚችሉ ዜጎችን እውቅና የሚሰጥ የምዘና ስረዓት ነው።
Recent News
Follow Us