News Detail
Oct 31, 2020
628 views
የትምህርት ሚኒስቴር በስነ ምግባር የታነፀ ትውልድ ለመፍጠር በሚያደረገው ጥረት ውስጥ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሙሉ ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለፀ።
"መምህራን ቀውስ ለመቀልበስም ሆነ ለመጪው ጊዜ ብሩህነት ግንባር ቀደም ሚና አላቸው" በሚል ትምህርት ሚኒስቴር ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር ያዘጋጁት የመምህራን ቀን ዓመታዊ በዓል አውደ ጥናት በባህር ዳር ተካሂዷል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ እምየ ቢተው የትምህርት ሚኒስቴር በስነ ምግባር የታነፀ ትውልድ ለመፍጠር በሚያደረገው ጥረት ውስጥ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሙሉ ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።
ተማሪዎች፣ መምህራንና ትምህርትን በተመለከተ የሚወጡ ህጎችንና አዋጆችን በማየትና በማፅደቅ ቅድሚያ የሚሰጡትን በመለየት በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ገረመው ሁሉቃ (ፒ ኤች ዲ) በበኩላቸው የመምህራንን ጥቅማ ጥቅም ማስጠበቅ፣ ስልጠና፣ የሙያ ማሻሻያ፣ መረጣ፣ ጥራትና አግባብነት ላይ ጥናት ተጠንቶ ለፖሊሲ አውጪዎች ለማቅረብ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በትምህርት ዘርፉ ላይ የሚኖርን አላስፈላጊ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነትን ለማስቀረትም እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በዓውደ ጥናቱ የመምህርነት ሙያ ላይ ያተኮሩ እና በኮቪድ 19 ተፅዕኖ ላይ የመምህራን ሚናን የሚመለከቱ ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው ምክክር ተደርጎባቸዋል።
በዓውደ ጥናቱ የትምህርት ሚኒስቴር፣ የአማራ ክልል፣ የባህርዳር ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ አምስቱም የልህቀት ማዕከላት፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት፣ የመምህራን ማህበር ሃላፊዎች እንዲሁም የተማሪ ወላጅ ማህበር ተሳትፈዋል።