News Detail

የሀገር ውስጥ ዜና
Sep 06, 2025 22 views

በ2018 ዓ.ም. ትምህርት ቤቶች ከመስከረም 05/2018 ዓ.ም ጀምሮ የመማር ማስተማር ሥራ ይጀምራሉ ፤ትምህርት ሚኒስቴር ከ2018 የትምህርት ዘመን ጀምሮ በሁሉም ትምህርት ቤቶች ሞባይል ስልክ ፣ ታብሌትና ኤሌክትሮኒክስ ቁሰቀቁሶችን ይዞ ትምህርት ቤት መምጣት ተከልክሏል፡፡

የ2018 የትምህርት ዘመን የትምህርት ቤቶች አከፋፈት አስመልክቶ ትምህርት ሚኒስቴር ከክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች ጋር የበይነ-መረብ ምክክር ባደረገበት ወቅት የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አየለች እሸቴ እንደገለጹት የ2018 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሥራ ሰኞ መስከረም 5/ቀን 2018 ዓ.ም በይፋ ይጀመራል።
በትምህርት ካሌንደሩ መሠረት ዓርብ መስከረም 2 / 2018 ዓ.ም. ትምህርት ቤቶች ክፍት ሆነው መምህራንና ተማሪዎች ውይይት የሚያደርጉበትና መስከረም 5/2018 ዓ.ም ደግሞ በይፋ ለሚጀመረው የትምህርት ስራ ቅድመ ዝግጅት የሚያደርጉበት ቀን መሆኑንም ክብርት ወ/ሮ አየለች አስታውቀዋል፡፡
በ2018 የትምህርት ዘመን ባለፈው ዓመት ከትምህርት ገበታ ውጪ የሆኑ ተማሪዎችን ጨምሮ ሁሉም እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህጻናትና ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ ወላጆች፣ መምህራንና የዘርፉ ባለድርሻዎች የጀመሩትን የንቅናቄ ተግባር አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባና የትምህርት ቤት ምዝገባም እስከ መጨረሻው ቀን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የተማሪዎችን ሥነ ምግባር በተመለከተም ከ2018 የትምህርት ዘመን ጀምሮ በየትኛውም ክልልና የከተማ አስተዳደር የሚገኝ ተማሪ ተንቀሳቃሽ ስልክ ፣ ታብሌትና ማናቸውንም የትምህርት ስራ ላይ ተጽእኖ ሚያሳድሩና አዋኪ የሆኑ የኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁሶችን ይዞ መገኘት ክልክል መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታዋ አስገንዝበዋል፡፡
በበይነ መረብ በተካሄደው ምክክር የትምህርት ጥራትና ፕሮግራሞች መሻሻል መሪ ስራ አስፈጻሚ ዩሀንስ ወጋሶ (ዶ/ ር) የ2018 የትምህረትት ዘመን የትምህርት ቤቶችን አከፋፈት ጋር ተያይዞ የባለድርሻ አካላት ሚና ፣የትምህርት ቤቶች ዝግጅት፣ ምቹና ደህንነቱ የተጠበቀ የትምህርት አካባቢ በመፍጠር፣ በትምህርት ለትውልድና በሌሎችም ዙሪያ ስትራቴጂክ እቅድ አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል፡፡
በምክክር መድረኩ የተሳተፉ የክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎችና ምክትል ቢሮ ኃላፊዎች በበኩላቸው ለ2018 የትምህርት ዘመን አከፋፈት ፣በተማሪዎች ምዝገባ ፣ በትምህርት አጀማመር፣ በመማር ማስተማር ስራውና በተማሪዎች ስነ ምገባር ዙሪያ አፈጻጸሞቻቸውን አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል።
Recent News
Follow Us